Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ዜና መዋዕል 22 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ዳዊትም፦ “ይህ የጌታ የእግዚአብሔር ቤት ነው፥ ይህም ለእስራኤል የሚቃጠለው መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ ነው” አለ።


ንጉሥ ዳዊት መቅደሱን ለመሥራት መዘጋጀቱ

2 ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች እንዲሰበስቡ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች እንዲወቅሩ ጠራቢዎችን አኖረ።

3 ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ።

4 ሲዶናውያውንና የጢሮስ ሰዎች ብዙ የዝግባ እንጨት ወደ ዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር የሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ።

5 ዳዊትም እንዲህ ብሏልና፦ “ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፥ ለጌታም የሚሠራው ቤት በአገሩ ሁሉ በስሙና በክብሩ እጅግ ታላቅና ዝነኛ ሊሆን ይገባል፤ እኔም ስለዚህ ዝግጅትን አደርጋለሁ።” ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ የግንባታ ቁሳቁስ አዘጋጀ።


ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንንና ሹማምንቱን ማዘዙ

6 ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ስም ቤት እንዲሠራ አዘዘው።

7 ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ፦ “ልጄ ሆይ! እኔ ለአምላኬ ለጌታ ቤት እንድሠራ በልቤ አስቤ ነበር።

8 ነገር ግን የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ ‘እጅግ ደም አፍስሰሃል፥ ታላቅም ውግያ አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም።

9 እነሆ፥ ልጅ ይወለድልሃል፤ እርሱም ሰላም ያለው ሰው ይሆናል፤ በዙሪያው ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ።

10 እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ ልጅም ይሆነኛል፥ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጸናለሁ።’

11 አሁንም፥ ልጄ ሆይ! ጌታ ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፥ የአምላክህንም የጌታን ቤት ሥራ።

12 ብቻ የአምላክህን የጌታን ሕግ እንድትጠብቅ ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፥ በእስራኤልም ላይ ያሰልጥንህ።

13 ጌታ ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዓትና ፍርድ ለመፈጸም ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ።

14 አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለጌታ ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ በሚዛንም የማይመዘን ብዙ ናስና ብረት አዘጋጀሁ፤ ደግሞም እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጀሁ፥ አንተም በዚያ ላይ ጨምርበት።

15 በአንተም ዘንድ ብዙ ሠራተኞች፥ ድንጋይ ወቃሪዎችና እንጨት ጠራቢዎች፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎች ሁሉ አሉህ።

16 የሚሠሩበት ወርቅና ብር ናስና ብረት ቍጥር የለውም፤ ተነሥተህ ሥራ፥ ጌታም ከአንተ ጋር ይሁን።”

17 ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን እንዲያግዙት የእስራኤልን ሹማምንት ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦

18 “አምላካችሁ ጌታ ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በጌታና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል።

19 አሁንም አምላካችሁን ጌታን ለመሻት ልባችሁንና ነፍሳችሁን ለእርሱ አሳልፋችሁ ስጡ፤ ለጌታም ስም ወደሚሠራው ቤት የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ለማምጣት ተነሥታችሁ የጌታን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos