Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤፌሶን 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገር

1 እናንተ በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤

2 በዚህም የዚህን ዓለም አኗኗር በመከተል፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው፥ በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።

3 በእነዚህም ልጆች መካከል እኛም ሁላችን፥ የሥጋችንንና የህዋሳቶቻችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበር፤ ደግሞም እንደ ሌሎቹ በባሕርያችን የቁጣ ልጆች ነበርን።

4 ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ እኛን ከወደደበት ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ፥

5 በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለን ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።

6 ደግሞም ከክርስቶስ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን፤

7 ይኸውም በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት መለኪያ የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ሊያሳይ ነው።

8 ጸጋው በእምነት አድኗችኋልና፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ የመጣም አይደለም።

9 ማንም እንዳይመካ ከሥራ የመጣም አይደለም።

10 እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ በሕይወት እንድንመላለስ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።


በክርስቶስ አንድ ነን

11 ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፥ “ተገርዘናል” በሚሉት፥ “ያልተገረዛችሁ” የተባላችሁትን ያን አስታውሱ፤

12 በዚያ ዘመን በዚህም ዓለም ያለ ክርስቶስ ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ፥ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ፥ ተስፋን አጥታችሁና ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ እንደ ነበር አስታውሱ።

13 አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል።

14 በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፥ ሁለቱን አንድ ያደረገ፥ እርሱ ሰላማችን ነውና፤

15 ሕግን ከትእዛዛቱና ከሥርዓቱ ጋር ሻረ፤ ከሁለቱ አንድ አዲስ ሕዝብ ፈጥሮ ሰላምን አደረገ፤

16 ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለቱን ሕዝቦች በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ።

17 መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን ሰበከ፤

18 በእርሱም አማካኝነት ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት እንችላለን።

19 እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ዜጎችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ ባዕዶችና መጻተኞች አይደላችሁም።

20 በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤

21 በእርሱ ሕንጻ ሁሉ አንድ ላይ ተገጣጥሞ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል።

22 በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos