ኢሳይያስ 42:5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርሷ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አዲሱ መደበኛ ትርጒም ሰማያትን የፈጠረ፣ የዘረጋቸውም፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ያበጀ፣ ለሕዝቧ እስትንፋስን፣ ለሚኖሩባትም ሕይወትን የሚሰጥ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሰማይን የፈጠረና ከዳር እስከ ዳር የዘረጋው፥ ምድርንና በውስጥዋ የሚኖሩትን ሁሉ የሠራ፥ ሕይወትንና እስትንፋስንም የሰጣቸው፥ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሰማይን የፈጠረ፥ የዘረጋውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ሁሉ ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ |
ከዚህ በኋላ ጌታ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፥ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፥ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።
“አቤቱ የሠራዊት ጌታ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል።
ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው?
እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፥ በእርሷም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥
ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በክህሎቱ ብርታት አንድ እንኳ አይጎለውም።
ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ ጌታ እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?
ሰማያትን የፈጠረ ጌታ፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፦ እኔ ጌታ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።
ምድሪቱን በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤ ለዓይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ።
‘አቤቱ ጌታ ሆይ! ወዮ! እነሆ፥ በእውነት አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፥ ለአንተም ከቶ የሚሳንህ ምንም ነገር የለም።
ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ “ይህችን ነፍስ በፈጠረልን በሕያው ጌታ እምላለሁ! አልገድልህም፥ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም” ብሎ በድብቅ ለኤርምያስ ማለ።
አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም ጌታ ነው።