ኢዮብ 33 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 “እንግዲህ፥ ኢዮብ ሆይ፥ ንግግሬን እንድትሰማ፥ ቃሌንም ሁሉ እንድታደምጥ እለምንሃለሁ። 2 እነሆ፥ ለመናገር ተዘጋጅቻለሁ፥ አንደበቴም ቃላትን አሰናድቷል። 3 ቃሎቼ የልቤን ቅንነት ያሳያሉ፥ ከንፈሮቼም የሚያውቁትን በቅንነት ይናገራሉ። 4 የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ። 5 ይቻልህ እንደሆነ መልስልኝ፥ የምትለውን አዘጋጅተህ በፊቴ ቁም። 6 እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ እኔም እንዳንተ ከጭቃ የተቀረጽሁ ነኝ። 7 እነሆ፥ ግርማዬ አያስፈራህም፥ እኔም አልጫንህም።” 8 “በጆሮዬ ተናግረሃል፥ የቃልህንም ድምፅ ሰምቻለሁ፤ እንዲህም ብለሃል፦ 9 ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፥ በደል የለብኝም፤ ያለ እንከን ነኝ፥ ኃጢአትም የለብኝም፥ 10 እነሆ፥ ሊወቅሰኝ ምክንያት ይፈጥራል፥ እንደ ጠላቱም ይቈጥረኛል፥ 11 እግሬን በግንዶች መካከል ያጣብቃል፥ መንገዶቼን ሁሉ ይቆጣጠራል።’ 12 እነሆ፥ አንተ በዚህ አቋምህ ትክክል አይደለህም፥ ‘እግዚአብሔር ከሰው ይበልጣል’ ብዬ እመልስልሃለሁ። 13 አንተ፦ ‘በፍጹም ለቃሌ መልስ አይሰጥም’ ብለህ፥ ስለምን ከእርሱ ጋር ትከራከራለህ? 14 እግዚአብሔር በአንድም በሁለትም መንገድ ይናገራል፥ ሰው ግን አያስተውለውም። 15 በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥ 16 በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥ በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥ 17 ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ፥ ሰውንም ከትዕቢት ይቆጥበው ዘንድ፥ 18 ነፍሱን ከጉድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል።” 19 “ደግሞ በአልጋ ላይ በስቃይ ይገሥጸዋል፥ አጥንቱም ሁሉ ያለማቋረጥ ይንቀጠቀጣል። 20 ሕይወቱም እንጀራን፥ ነፍሱም ጣፋጭ መብልን ትጠላለች። 21 ሥጋው እስከማይታይ ድረስ ይሰለስላል፥ ተሸፍኖ የነበረውም አጥንት ይገለጣል። 22 ነፍሱ ወደ ጉድጓዱ፥ ሕይወቱም ወደሚገድሉአት ቀርባለች። 23 የቀናውን መንገድ ለሰው ያስታውቀው ዘንድ፥ ከሺህ አንድ ሆኖ የሚተረጉም መልአክ ቢገኝለት፥ 24 እየራራለት፦ እሱን መታደጊያ ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ መቃብር እንዳይወርድ አድነው ቢለው፥ 25 ሥጋው እንደ ልጅ ሥጋ ይለመልማል፥ ወደ ወጣትነቱም ጊዜ ይመለሳል። 26 ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ እርሱም ይሰማዋል፥ ፊቱንም በደስታ ያሳየዋል፥ ለሰውም የጽድቁን ዋጋ ይመልስለታል። 27 እርሱም በሰው ፊት እየዘመረ፦ እኔ በድያለሁ፥ ቀናውንም አጣምሜአለሁ፥ የሚገባኝንም ቅጣት አልተቀበልሁም፥ 28 ነፍሴ ወደ መቃብር እንዳትወርድ አድኖአታል፥ ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች ይላል።” 29 “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ሁለት ጊዜና ሦስት ጊዜ ከሰው ጋር ያደርጋል፥ 30 ይህም ነፍሱን ከመቃብር ይመልስ ዘንድ፥ በሕያዋንም ብርሃን ያበራ ዘንድ ነው። 31 ኢዮብ ሆይ፥ አድምጥ፥ እኔንም ስማ፥ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ። 32 የምትናገረው ቢኖርህ መልስልኝ፥ ትክክል መሆንህን እወድዳለሁና ተናገር። 33 አለበለዚያም እኔን ስማ፥ ዝም በል፥ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።” |