ሕዝቅኤል 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የግል ቅጣት 1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 አባቶች ጎምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች አጠረሰ፥ ብላችሁ ስለ እስራኤል ምድር የምትመስሉት ምሳሌ ምንድነው? 3 እኔ ሕያው ነኝ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እንግዲህ ወዲህ ይህ ምሳሌ በእስራኤል ውስጥ በእናንተ አይመሰልም። 4 እነሆ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፥ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች የልጅም ነፍስ የእኔ ናት፥ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች። 5 ሰው ጻድቅ ቢሆን፥ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ 6 በተራሮች ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹን ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውን ሚስት ባያረክስ፥ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፥ 7 ማንንም ሰው ባያስጨንቅ፥ ነገር ግን ለባለ ዕዳው መያዣውን ቢመልስ፥ ባይቀማ፥ ከምግቡ ለተራበ ቢሰጥ፥ የተራቆተውንም በልብስ ቢሸፍን፥ 8 በአራጣ ባያበድር፥ ትርፍ ባይወስድ፥ እጁንም ከበደል ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነተኛ ፍትሕ ቢያደርግ፥ 9 በትእዛዜ ቢሄድ፥ እውነትን ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፥ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 10 እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ፥ ከእነዚህም አንዱን የሚያደርግ ልጅ ቢወልድ፥ 11 እርሱም እነዚህን ሁሉ ባይሠራ፥ በተራራም ላይ ቢበላ፥ የባልንጀራውን ሚስት ቢያረክስ፥ 12 ድሀውንና ችግረኛውን ቢያስጨንቅ፥ ቢቀማ፥ መያዣውን ባይመልስ፥ ዐይኖቹን ወደ ጣዖታት ቢያነሣ፥ ርኩሰትን ቢያደርግ፥ 13 በአራጣ ቢያበድር፥ ትርፍንም ቢወስድ፥ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም፤ እነዚህን ርኩሰቶች ሁሉ አድርጎአልና በእርግጥ ይሞታል፤ ደሙም በላዩ ላይ ይሆናል። 14 እነሆም ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት ቢያይ፥ ቢፈራ፥ እነዚህንም ባይሠራ፥ 15 በተራራ ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥ 16 ሰውን ባያስጨንቅ፥ መያዣውን ባይወስድ፥ ባይቀማ፥ ከምግቡ ለተራበ ቢሰጥ፥ የተራቆተውንም በልብስ ቢሸፍን፥ 17 ድሀ ከመበደል እጁን ቢመልስ፥ አራጣ ወይም ትርፍ ባይወስድ፥ ፍርዴን ቢያደርግ፥ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኃጢአት አይሞትም። 18 አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ቀምቶአልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ፥ እርሱ በበደሉ ይሞታል። 19 እናንተ ግን፦ የአባትን ኃጢአት ልጁ ለምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅና ቢያደርገው በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። 20 ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች፥ ልጅ የአባትን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጅን ኃጢአት አይሸከምም፥ የጻድቅ ሰው ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የክፉ ሰው ክፋትም በራሱ ላይ ይሆናል። 21 ክፉ ሰው ከሠራው ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 22 የሠራው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፥ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል። 23 በውኑ በኃጢአተኛው ሞት እደሰታለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ከመንገዱስ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለምን? 24 ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ፥ በደልንም ቢሠራ፥ ክፉ ሰው እንደሚያደርገው ርኩሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራው ጽድቅ ሁሉ አይታሰብለትም፤ ታማኝ ባለመሆኑና በሠራው ኃጢአት በእነሱ ይሞታል። 25 እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ ቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ ስሙ፥ በውኑ መንገዴ ቀና አይደለምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን? 26 ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ በደልንም ቢሠራ፥ በዚያ ቢሞት፥ እርሱ በሠራው በደል ይሞታል። 27 ክፉ ሰውም ከሠራው ክፋት ቢመለስ፥ ፍትሕንና ጽድቅንም ቢያደርግ ነፍሱን በሕይወት ያኖራል። 28 የሠራውን በደል ሁሉ አይቶ ተመልሶአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 29 ሆኖም የእስራኤል ቤት የጌታ መንገድ ቀና አይደለም ይላሉ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ መንገዶቼ ቀና አይደሉምን? ቀና ያልሆኑትስ የእናንተ መንገዶች አይደሉምን? 30 ስለዚህ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እያንዳንዱን ሰው እንደ መንገዱ እፈርዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ተመለሱ፥ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። 31 የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፥ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ለምን ትሞታላችሁ? 32 የሟቹ ሞት አልደሰትምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ። |