ኢዮብ 34 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ኤሊሁም ደግሞ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ 2 “እናንተ ጥበበኞች፥ ቃሌን ስሙ፥ እናንተም አዋቂዎች፥ ወደ እኔ አድምጡ። 3 ምላስ መብልን እንደሚያጣጥም፥ ጆሮም ቃላትን ይለያልና። 4 ፍትሕን እንምረጥ፥ መልካሙንም ነገር በመካከላችን እንወቅ። 5 ኢዮብ፦ እኔ ንጹሕ ነኝ፥ እግዚአብሔር ግን ፍርድ ከለከለኝ፥ 6 ምንም እውነተኛ ብሆን እንደ ውሸተኛ ተቈጠርሁ፥ ምንም ባልበድል ቁስሌ የማይፈወስ ነው ብሏል። 7-9 ኢዮብም፦ በእግዚአብሔር መደሰት ለሰው ምንም አይጠቅምም ብሏልና፥ ከበደለኞች ጋር የሚተባበር፥ ክፉ ከሚያደርጉስ ጋር የሚሄድ፥ ሹፈትን እንደ ውኃ የሚጠጣት እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?” 10 “ስለዚህ የምታስተውሉ ሰዎች፥ ስሙኝ፥ ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር፥ በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ። 11 ለሰው እንደ ሥራው ይመልስለታል፥ ሰውም እንደ መንገዱ ያገኝ ዘንድ ያደርጋል። 12 በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም። 13 ምድርን አደራ የሰጠው ማን ነው? ዓለምንስ ሁሉ በእርሱ ላይ ያኖረ ማን ነው? 14 እርሱ ልቡን ወደ ራሱ ቢመልስ፥ መንፈሱንና እስትንፋሱን ወደ ራሱ ቢሰበስብ፥ 15 ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፥ ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል።” 16 “አስተዋይ ከሆንክ ይህን ስማ፥ ንግግሬንም አድምጥ። 17 በውኑ ጽድቅን የሚጠላ ሊገዛ ይገባዋልን? ጻድቅና ኃያል የሆነውንስ በደለኛ ታደርገዋለህን? 18 ማንም ሰው ንጉሡን፦ በደለኛ ነህ፥ መኰንኖቹን፦ ክፉዎች ናችሁ ይላልን? 19 እነርሱ ሁሉ የእጁ ሥራ ናቸውና ለአለቆች አያደላም፥ ሀብታሙንም ሰው ከድሀው ይበልጥ አይመለከትም። 20 እነርሱ በእኩለ ሌሊት በድንገት ይሞታሉ፥ ሕዝቡ ተንቀጥቅጦ ያልፋል፥ ኃያላንም ያለ ምንም ድካም ይወገዳሉ። 21 ዐይኖቹ የሰውን መንገድ ይመለከታሉ፥ የሰውን እርምጃ በሙሉ ያያል። 22 ክፋትን የሚሠሩ የሚደበቁበት ጨለማ ወይም የሞት ጥላ የለም። 23 ሰው ወደ እግዚአብሔር ለፍርድ ለመቅረብ ቀጠሮ አይሰጠውም። 24 ኃያላንን ያለ ምርመራ ይሰባብራል፥ በእነርሱም ፋንታ ሌሎችን ያቆማል። 25 ሥራቸውን ያውቃል፥ በሌሊት ይገለባብጣቸዋል፤ እነርሱም ይደቃሉ። 26 ሰዎች እያዩ እንደ ክፉዎች ይመታቸዋል፥ 27-28 የድሀውን ልቅሶ እስኪሰማ ድረስ፥ የችግረኛውን ድምፅ እስኪሰማ ድረስ፥ እርሱን ከመከተል ርቀዋልና፥ ከመንገዱም አንዱንም አልተመለከቱምና። 29 ሕዝብንም ሆነ ሰውን በተመለከተ፥ ዝም ቢል የሚፈርድ ማን ነው? ፊቱንስ ቢሰውር የሚያየው ማን ነው? 30 ይህም እግዚአብሔርን የሚክድ እንዳይነግሥ፥ በሕዝቡም ላይ ወጥመድ የሚዘረጋ እንዳይኖር ነው። 31 እግዚአብሔርን፦ እኔ ሳልበድል ቅጣት ተቀበልሁ፥ 32 የማላየውን ነገር አንተ አስተምረኝ፥ ኃጢአትንም ሠርቼ እንደሆነ፥ ደግሜ አልሠራም የሚለው ማን ነው? 33 በውኑ አንተ ተቃውመኸዋልና ሽልማቱ አንተ እንደምትወድደው ይሆናልን? እኔ ሳልሆን አንተ ነህ የምትመርጠው፥ ስለዚህ የምታውቀውን ተናገር። 34 የሚሰሙኝ ጥበበኞች ሁሉ፥ አስተዋዮችም እንዲህ ይሉኛል፦ 35 ኢዮብ ያለ እውቀት ተናግሮአል፥ ንግግሩም ማስተዋል ይጎድለዋል። 36 ኢዮብ እስከ መጨረሻ ድረስ ምነው በተፈተነ ኖሮ! እርሱ እንደ ክፉዎች መልሶአልና፥ 37 በኃጢአቱም ላይ ዓመፅን ጨምሮአልና፥ በእኛም መካከል በፌዝ ያጨበጭባልና፥ እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ቃላትን ያበዛልና።” |