Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 37 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሕዝቅያስ ኢሳይያስን ማማከር

1 ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ ጌታም ቤት ገባ።

2 የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው።

3 እነርሱም፦ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል ለመውለድም ብርታቱ የለም።

4 ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ አለቃው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ ጌታ ሰምቶ እንደሆነ፥ አምላክህ ጌታም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደሆን፥ ስለዚህ አንተም በሕይወት ስለተረፉት ቅሬታ ጸልይ አሉት።”

5 ከዚያም የንጉሡ የሕዝቅያስ አገልጋዮች ወደ ኢሳይያስ መጡ።

6 ኢሳይያስም፥ “ለአለቃችሁ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ።

7 እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም ላይ በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት’ ” አላቸው።

8 ራፋስቂስም ተመለሰ፤ የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ስለ ነበር በልብና ከተማ ሲዋጋ አገኘው።

9 የአሦርም ንጉሥ፦ “የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊዋጋህ መጥቷል” የሚል ወሬ ሰማ። ይህን በሰማም ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥ እንዲህም አለው፦

10 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክ አያታልህ።

11 እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን?

12 አባቶቼ ያጠፉአቸውን ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፍስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸው?

13 የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ?”

14 ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ጌታ ቤት ሕዝቅያስም ወጥቶ በጌታ ፊት ዘረጋው።

15 ወደ ጌታ እንዲህ በማለት ሕዝቅያስ ጸለየ፦

16 “አቤቱ የሠራዊት ጌታ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል።

17 ጌታ ሆይ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ ጌታ ሆይ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ለመገዳደር የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ።

18 ጌታ ሆይ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት ዓለሙን ሁሉ አገሮቻቸውንም አፍርሰዋል፤

19 አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ፥ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል።

20 እንግዲህም አምላካችን ጌታ ሆይ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ ጌታ እንደሆንህ እንዲያውቁ ከእጁ አድነን።”

21 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ለምነሀልና

22 ጌታ ስለ እርሱ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፥ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ስትሸሽ ራስዋን ነቅንቃብሃለች።

23 የተገዳደርኸው የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደርግህበት፥ ዓይንህንስ ወደ ላይ ያነሣህበት ማን ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ አይደለምን!’

24 አንተም እንዲህ አለክ፦ በሠረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሲባኖስ ጥግ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹን ዝግባዎች፥ የተመረጡትን ጥንዶች እቈርጣለሁ፥ ወደ ከፍታውም ዳርቻ ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ፤

25 ቈፈርኩ ውኃም ጠጣሁ፥ የግብጽንም ወንዞች ሁሉ በእግሬ ጫማ አደረቅኩ።”

26 ይህን እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? እሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግኩ።

27 ስለዚህ የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሏል፥ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለመለመም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታውም እህል ሆነዋል።

28 እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህን መግቢያህንም በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቁጣ አውቄአለሁ።

29 ቁጣህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአል፤ ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፤ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ።

30 ይህ ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ ታጭዳላችሁ፤ ወይንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።

31 የተረፈው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፥ ወደ ላይም ያፈራል።

32 ከኢየሩሳሌም ቅሬታ፥ ከጽዮን ተራራ ያመለጡት ይመጣሉ፤ የሠራዊት ጌታ ቅንዓት ይህን ያደርጋል።

33 “ስለዚህም ጌታ ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ወደዚች ከተማ አይመጣም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም አይደለድልባትም።

34 በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፤ ወደዚችም ከተማ አይመጣም፥ ይላል ጌታ።

35 ስለ እኔም ስለ አገልጋዬም ዳዊት ይህችን ከተማ አድናታለሁ፥ እጋርዳታለሁም።”


የሰናክሬም ሽንፈትና ሞት

36 የጌታም መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ።

37 የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፤ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ።

38 በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos