ዘዳግም 16:19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ፍርድ አታዛባ፤ አድልዎ አታድርግ፤ ጉቦ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦም አትቀበል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ፍርድ አታዛባ፤ አድልዎ አታድርግ፤ ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህ አታድላ፤ አታታል፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዐይን ስለሚያሳውርና የተጣመመ ፍርድ ስለሚያሰጥ ጉቦ አትቀበል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህም አታድላ፤ ጉቦን አትቀበል፥ ጉቦ የጥበበኞችን ዐይን ያሳውራልና፥ የእውነትንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ፍርዱን አታጣምም፤ ፊት አይተህም አታድላ፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል። |
አንተም ከሕዝቡ ሁሉ መስራት የሚችሉ፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፥ የታመኑ፥ የጉቦ ትርፍን የሚጠሉ ሰዎችን ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የዐሥር አለቆችን ሹምላቸው።
ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጉቦን ይወዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም።
በጽድቅ የሚሄድ ቅን ነገርንም የሚናገር፥ በጭቆና የሚገኝ ትርፍን የሚጸየፍ፥ መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚሰበስብ፥ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮቹን የሚከልል፥ ክፋትንም ከማየት ዐይኖቹን የሚጨፍን ነው።
ወፍረዋል ሰብተዋልም፥ ክፋታቸውንም ያለ ልክ አብዝተዋል፤ የድሀ አደጎች ነገር መልካም እንዲሆንላቸው አልተምዋገቱላቸውም፥ የችግርተኞችንም ፍርድ አልፈረዱላቸውም።
ደም ለማፍሰስ በአንቺ ውስጥ ጉቦን ተቀበሉ፥ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ጎረቤቶችሽንም ጨቁነሽ የማይገባ ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
እጆቻቸው ክፉ ለማድረግ የተለማመዱ ናቸው፤ ልዑሉና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፤ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጉናሉ።
ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ በእውነት አስተዋልሁ።
ጳውሎስ ግን “እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን? አይሆንም፤ ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን፤” አላቸው።
በዚያን ጊዜ ጳውሎስ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ! እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን?” አለው።
ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ፥ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ፥ ኃያልም፥ የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ ጉቦም የማይቀበል ነው።
እነሆ፤ ከፊታችሁ ቆሜአለሁ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንን አህያ ወሰድሁ? ማንን አታለልሁ? በማንስ ላይ ግፍ ሠራሁ? አይቶ እንዳላየ ለመሆንስ ከማን እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? ከእነዚህ ሁሉ አንዱን እንኳ አድርጌ ከሆነ እመልስላችኋለሁ።”