Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ምሳሌ 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 በክፉ ሰዎች አትቅና፥ ከእነርሱ ጋርም መሆንን አትመኝ፥

2 ልባቸው ግፍን ታስባለችና፥ ከንፈራቸውም ተንኮልን ትናገራለችና።

3 ቤት በጥበብ ይሠራል፥ በማስተዋልም ይጸናል፥

4 በእውቀት የቤት ክፍሎች በከበረውና ባማረው ሀብት ሁሉ ይሞላሉ።

5 ጠቢብ ሰው ብርቱ ነው፥ አዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል።

6 በመልካም አመራር ጦርነትን ትመራለህ፥ ብዙ ምክር ባለበትም ድል ይገኛል።

7 ጥበብ ለሞኝ ሰው ከፍ ብላ የራቀች ናት፥ በከተማውም በር ላይ መናገር አይችልም።

8 ክፉ ለማድረግ የሚያውጠነጥን፥ ተንኰለኛ ይባላል።

9 የሞኝ እቅድ ኃጢአት መሥራት ነው። ሰዎች ፌዘኛውን ይጸየፉታል።

10 በመከራ ቀን ብትዝል፥ በእርግጥም ጉልበትህ ትንሽ ነው ማለት ነው።

11 ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፥ ለመታረድ የተወሰነባቸውን አድን።

12 እነሆ፥ ይህን አላውቀውም ብትል፥ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን?

13 ልጄ ሆይ፥ መልካም ነውና ማር ብላ፥ ወለላም ለጣምህ ጣፋጭ ነው።

14 ጥበብም ለነፍስህ እንዲሁ እንደሚሆን እወቅ፥ ብታገኘውም ፍጻሜህ መልካም ይሆናል፥ ተስፋህም አይጠፋም።

15 እንደ ክፉ ሰው በጻድቅ ቤት ላይ አትሸምቅ፥ ማደሪያውንም አታውክ።

16 ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፤ ደግሞም ይነሣል፥ ክፉዎችን ግን መጥፎ ነገር ሲገጥማቸው ይወድቃሉ።

17 ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ፥

18 ጌታ ይህንን አይቶ እንዳያዝንብህ፥ ቁጣውንም ከእርሱ ላይ እንዳያነሣ።

19 በክፉ አድራጊዎች የተነሣ አትቈጣ፥ በክፉዎችም አትቅና።

20 ለክፉ ሰው የወደፊት ተስፋ የለውምና፥ የክፉዎች መብራት ይጠፋልና።

21 ልጄ ሆይ፥ ጌታንና ንጉሥን ፍራ፥ ከዓመፀኞችም ጋር አትደባለቅ።

22 መከራቸው ድንገት ይነሣልና፥ ከሁለቱ የሚመጣውን ጥፋት ማን ያውቃል? (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።) የነገሩትን የሚሰማ ልጅ ከጥፋት የራቀ ነው፥ የነገሩትን የሚቀበልን ሰው እግዚአብሔር ይቀበለዋል። ከንጉሥ አንደበት ምንምን ሐሰት ይነገራል አይባልም፥ ከአንደበቱም የሚወጣ ሐሰት የለም። የንጉሥ ቃል ሾተል ናት፥ ለጥፋት የተሰጠችውን ሰው ሰውነት ታጠፋዋለች እንጂ አንድ አካል ብቻ የምታጠፋ አይደለም። ሰይፈ መዓቱ ብትሳል ግን ከወገኑ ጋር ሰውን ታጠፋለች፥ ከአሞሮች ግልገል ወገን የማይበላ እስኪሆን ድረስ እንደ እሳት ነበልባል ታቃጥላለች።

23 እነዚህ ደግሞ የጠቢባን ቃሎች ናቸው። በፍርድ ላይ ማዳለት መልካም አይደለም።

24 ክፉዉን፦ “ጻድቅ ነህ” የሚለውን ወገኖች ይረግሙታል አሕዛብም ይጠሉታል፥

25 የሚዘልፉት ግን ደስታ ይሆንላቸዋል፥ በላያቸውም መልካም በረከት ትመጣላቸዋለች።

26 በቀና ነገር የሚመልስ በፍቅር ይሰማል።

27 ሥራህን በውጭ አሰናዳ፥ ለራስህ በእርሻ ውስጥ አዘጋጀው፥ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ።

28 በባልንጀራህ ላይ በከንቱ ምስክር አትሁን፥ በከንፈርህም አታባብለው።

29 እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፥ እንደ ሥራውም እበቀለዋለሁ አትበል።

30 በሰነፍ ሰው እርሻ፥ አእምሮ በጐደለውም ሰው ወይን ቦታ አለፍሁ።

31 እነሆም፥ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፥ ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል፥ የድንጋዩም ቅጥር ፈርሶአል።

32 ተመለከትሁና አሰብሁ፥ አየሁትና ተግሣጽን ተቀበልሁ።

33 ትንሽ መተኛት፥ ትንሽ ማንቀላፋት፥ ለማረፍ እጅህን ታጥፋለህ፥

34 እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። (በግዕዝ መጽሐፈ ተግሣጽ ይባላል)።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos