ሕዝቅኤል 22 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ደም አፍሳሽ ከተማ 1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርዳለህን? ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኩሰትዋን ሁሉ አስታውቃት። 3 እንዲህም በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከልዋ ደምን የምታፈስ ከተማ ሆይ!ጊዜዋ ደርሶአል፥ እንድትረክስም በራስዋ ላይ ጣዖታትን የምታደርግ፤ 4 ባፈሰስሽው ደም በድለሻል፥ በሠራሻቸውም ጣዖቶችሽ ረክሰሻል፥ ቀንሽን አቀረብሽ፥ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፥ ስለዚህ ለሕዝቦች መሰደቢያ፥ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ። 5 አንቺ ስምሽ የረከሰ፥ ሽብር የሞላብሽ ሆይ፥ ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል። 6 እነሆ የእስራኤል ልዑሎች እያንዳንዱ እንደ አቅሙ ደም ሊያፈስሱ በአንቺ ውስጥ ነበሩ። 7 አባትንና እናትን አቃለሉ፥ በመካከልሽ መጻተኛውን ጨቆኑ፥ በአንቺ ውስጥ የሙት ልጅንና መበለቲቱን አስጨነቁ። 8 ቅዱሳን ነገሮቼን ናቅሽ፥ ሰንበቶቼን አረከስሽ። 9 ሐሜተኞች ሰዎች ደምን ሊያፈስሱ በአንቺ ውስጥ ነበሩ፥ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፥ በመካከልሽ ሴሰኝነትን አደረጉ። 10 በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ዕራቁትነት ገለጡ፥ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ። 11 ሰውም ከጎረቤቱ ሚስት ጋር ርኩሰትን አደረገ፥ ሌላውም የልጁን ሚስት በዝሙት አረከሰ፥ ሌላውም በአንቺ ውስጥ የአባቱን ልጅ፥ እኅቱን አዋረደ። 12 ደም ለማፍሰስ በአንቺ ውስጥ ጉቦን ተቀበሉ፥ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ጎረቤቶችሽንም ጨቁነሽ የማይገባ ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 13 እነሆ ያለ አግባብ በአገኘሽው ትርፍና በመካከልሽ በፈሰሰው ደም ላይ እጄን አጨበጨብሁ። 14 ከአንቺ ጋር በምነጋገርበት ጊዜ ልብሽ መቋቋም ይችላልን? እጆችሽስ ይጸናሉን? እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፥ አደርገዋለሁም። 15 ወደ አገሮች እበትንሻለሁ፥ በምድርም እዘራሻለሁ፥ ርኩሰትሽንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ። 16 በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቂአለሽ። 17 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18 የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ለእኔ እንደ አተላ ሆኑብኝ፥ እነርሱ ሁሉ በከውር ውስጥ መዳብና ቆርቆሮ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ የብር ዝቃጭ ናቸው። 19 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁላችሁ የብረት ዝቃጭ ሆናችኋልና፥ ስለዚህ እነሆ፥ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰብስባችኋለሁ። 20 ሰው ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቆርቆሮንም ለማቅለጥ እሳትን ሊያነድበት በማቅለጫ እንደሚሰበስብ፥ እንዲሁ በቁጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፥ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ። 21 እሰበስባችሁአለሁ፥ የመዓቴንም እሳት አነድባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ። 22 ብርም በማቅለጫ ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፥ እኔም ጌታ መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ። 23 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24 የሰው ልጅ ሆይ እንዲህ በላት፦ አንቺ ያልነጻሽ፥ በቁጣም ቀን ያልዘነበብሽ ምድር ነሽ በላት። 25 በውስጧ ያሉ ነቢያት እንደሚጮኽና የገደለውን እንደሚበላ አንበሳ ናቸው፤ ነፍሶችን በልተዋል፥ ሀብትንና የከበሩ ነገሮችን ወስደዋል፤ በውስጧም ብዙዎችን መበለቶች አድርገዋል። 26 ካህናቶችዋም ሕጌን ጥሰዋል፥ ቅዱሳት ነገሮቼንም አርክሰዋል፤ ቅዱስ በሆነ ነገርና በረከሰ ነገር ላይ ልዩነትን አላደረጉም፥ በርኩስ ነገርና በንጹሕ ነገር መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም፥ ከሰንበቶቼ ዓይናቸውን ሰወሩ፥ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ። 27 በውስጧ ያሉ አለቆችዋ የገደሉትን እንደሚቦጫጭቁ ተኩላዎች ናቸው። ተገቢ ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሳሉ፥ ነፍሶችንም ያጠፋሉ። 28 ነቢዮችዋ ጌታ ሳይናገር “ጌታ እንዲህ ይላል” እያሉ የሐሰት ራእይ በማየትና በውሸት ሟርት፥ በኖራ ይለቀልቋቸዋል። 29 የምድሪቱ ሕዝብ ግፍ አደረጉ፥ ዝርፊያም ፈፀሙ፥ ድሃውንና ችግረኛውን አንገላቱ፥ መጻተኛውንም ያለ ፍትሕ በደሉ። 30 ቅጥሩን የሚሠራ፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም። 31 ስለዚህ ቁጣዬን አፈሰስሁባቸው፤ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |