ዘዳግም 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በዓለ ፋሲካ ( ዘፀ. 12፥1-20 ) 1 “በሚያዝያ ወር ከግብፅ ሀገር በሌሊት ወጥተሃልና የሚያዝያን ወር ጠብቀህ፥ የአምላክህ የእግዚአብሔርን ፋሲካ አድርግ። 2 አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራበት ዘንድ በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ፋሲካ ከበግና ከላም መንጋ ሠዋ። 3 የቦካውን እንጀራ ከእርሱ ጋር አትብላ፤ ከግብፅ ሀገር በችኮላ ስለ ወጣህ ከግብፅ ሀገር የወጣህበትን ቀን በዕድሜህ ሁሉ ታስብ ዘንድ የመከራን እንጀራ፥ ቂጣ እንጀራ ሰባት ቀን ከእርሱ ጋር ብላ። 4 ሰባት ቀንም በሀገርህ ሁሉ የቦካ አይታይም፤ በመጀመሪያው ቀን ማታ ከሠዋኸው ሥጋ እስከ ነገ ድረስ ምንም አይደር። 5 አምላክህ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከተሞች በማንኛዪቱም ፋሲካን ትሠዋ ዘንድ አይገባህም። 6 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ በመረጠው በዚያ ስፍራ ከግብፅ በወጣህበት ወራት፥ ፀሐይ ሲገባ፥ ማታ ፋሲካን ትሠዋለህ። 7 አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ትጠብሰዋለህ፤ ታበስለዋለህም፤ ትበላውማለህ፤ በነጋውም ተመልሰህ ወደ ቤትህ ትሄዳለህ። 8 ስድስት ቀን ቂጣ እንጀራ ብላ፤ ሰባተኛው ቀን ግን መውጫው ስለሆነ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በዓል ይሁን፤ ለነፍስም ከሚሠራው በቀር ሥራን ሁሉ አታድርግበት። የመከር በዓል፤ ( ዘፀ. 34፥22 ፤ ዘሌ. 23፥15-21 ) 9 “ሰባት ሳምንትም ትቈጥራለህ፤ መከሩን ማጨድ ከምትጀምርበት ቀን ጀምሮ ሰባት ሳምንት መቍጠር ትጀምራለህ። 10 አምላክህ እግዚአብሔር የባረከህን ያህል እጅህ መስጠት በምትችለው መጠን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሰባቱን ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ። 11 አንተ፥ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፥ ወንድ ባሪያህና ሴት ባሪያህ፥ በሀገርህም ውስጥ ያለው ሌዋዊ፥ በመካከልህም ያሉ መጻተኛና ድሃ-አደግ፥ መበለትም አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራበት ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 12 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ ዐስብ፤ ይህንም ሥርዐት ጠብቅ፤ አድርገውም። የዳስ በዓል ( ዘሌ. 23፥33-43 ) 13 “ከአውድማህና ከወይን መጭመቂያህ ፍሬህን በሰበሰብህ ጊዜ ሰባት ቀን የዳስ በዓል አድርግ። 14 አንተም፥ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፥ ወንድ ባሪያህና ሴት ባሪያህ፥ በሀገርህም ውስጥ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ፥ ድሃ-አደግና መበለትም በበዓልህ ደስ ይበላችሁ። 15 አምላክህ እግዚአብሔር ለራሱ በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰባት ቀን በዓል ታደርጋለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በፍሬህ ሁሉ፥ በእጅህም ሥራ ሁሉ ይባርክሃልና። አንተም ፈጽሞ ደስ ይልሃልና። 16 በዓመት ሦስት ጊዜ በቂጣ በዓል፥ በሰባቱ ሱባዔም በዓል፥ በዳስም በዓል ወንድ ልጅህ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ይታይ፤ 17 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጅህን አትታይ። አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ በረከት መጠን እያንዳንዳችሁ እንደ ችሎታችሁ ታመጣላችሁ። ስለ ፍርድ አሰጣጥ 18 “አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በሀገርህ ደጅ ሁሉ በየነገዶችህ ፈራጆችንና መባውን የሚጽፉትን ሹሙ፤ ለሕዝቡም ቅን ፍርድን ይፍረዱ። 19 ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህም አታድላ፤ ጉቦን አትቀበል፥ ጉቦ የጥበበኞችን ዐይን ያሳውራልና፥ የእውነትንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል። 20 በሕይወት ትኖር ዘንድ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም የሚሰጥህን ምድር ትወርስ ዘንድ እውነተኛውን ፍርድ ተከተል። የአምልኮ ጣዖት መከላከል 21 “ለአንተ በምትሠራው በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ አጠገብ ከማናቸውም ዛፍ የማምለኪያ ዐጸድ አድርገህ አትትከል። 22 አምላክህ እግዚአብሔርም የሚጠላውን ሐውልት ለአንተ አታቁም። |