ዕንባቆም 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የነቢዩ አቤቱታ 1 ነቢዩ ዕንባቆም ያየው ሸክም። 2 ጌታ ሆይ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? “ግፍ” ብዬ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም። 3 ክፉ ሥራ ለምን አሳየኸኝ? ድካምንስ ለምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብና ክርክር ይነሣሉ። 4 ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፥ ፍትሕ ድል ነሥቶ አይወጣም፤ ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና፤ ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል። 5 አሕዛብን እዩ፥ ተመልከቱም፤ እጅግ ተደነቁ፥ ተገረሙም፤ ቢነገራችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁና። 6 እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ለመውረስ በምድር ሁሉ ላይ የሚሄዱትን፥ መራሮችና ችኩሎች ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ። 7 እነርሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል። 8 ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፥ ከማታም ተኩላ ይልቅ አስፈሪዎች ናቸው፤ ፈረሰኞቻቸውም ይንሳፈፋሉ፥ ፈረሰኞቻቸው ከሩቅ ይመጣሉ፥ ለመንጠቅ እንደሚቸኩል ንስር ይበርራሉ። 9 ሁሉም ለዓመፅ ይመጣሉ፥ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ ያቀናሉ፤ ምርኮኞችን እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ። 10 በነገሥታት ላይ ያላግጣሉ፥ ገዢዎችም መሳቂያ ሆነውላቸዋል፤ በምሽጎቹ ሁሉ ይስቃሉ፥ አፈሩን ከምረው ይወስዱታል። 11 የዚያን ጊዜም እንደ ነፋስ ጠራርገው ይሄዳሉ፤ ኃይላቸውን አምላካቸው ያደረጉ በደለኞች ናቸው። 12 ጌታ አምላኬ፥ ቅዱሴ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፤ ጌታ ሆይ፥ ለፍርድ ወስነሃቸዋል፥ ዓለት ሆይ ለተግሣጽም መሠረትሃቸው። 13 ዐይኖችህ ክፉ እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው፥ ክፉ ሥራም መመልከት አትችልም፤ አታላዮችን ለምን ትመለከታለህ? ክፉዎቹ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆኑትን ሲውጡ ለምን ዝም ትላለህ? 14 ሰዎችን እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ ገዢ እንደሌላቸው የሚሳቡ ፍጥረቶች አደረግሃቸው። 15 ሁሉን በመንጠቆ ያወጣል፥ በመረቡ ይጎትታቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፤ ስለዚህ ደስ ይለዋል፥ ሐሤትም ያደርጋል። 16 ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል። በእነርሱ ድርሻው ሰብቷልና፥ መብሉም በዝቶአልና። 17 ስለዚህ መረቡን ባዶ ከማድረግና አሕዛብን ዘወትር ከመግደል አይቆጠብምን? |