Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘዳግም 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የፋሲካ በዓል
( ዘፀ. 12፥1-20 )

1 “አንተን ከግብጽ ምድር ያወጣህ ከአቢብ ወር ውስጥ በአንዱ ሌሊት ስለ ሆነ በዚህ ወር የፋሲካን በዓል በማድረግ እግዚአብሔር አምላክህን አክብር።

2 እግዚአብሔር አምላክህ ለስሙ መጠሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ እርሱን ለማክበር ከበጎችህና ከከብቶችህ መንጋዎች መርጠህ አንዳንድ ሠዋ፤

3 ያንንም ራት በምትመገብበት ጊዜ እርሾ የነካው እንጀራ አትብላ፤ በዚያ ዐይነት አስቸኳይ ሁኔታ ግብጽን ለቀህ በወጣህበት ጊዜ እንዳደረግኸው ሰባት ቀን ሙሉ እርሾ ያልነካው ቂጣ ትበላለህ፤ ይህን ቂጣ ብላ፤ እርሱም የሥቃይ እንጀራ ተብሎ ይጠራል፤ ይኸውም በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ብዙ ሥቃይ ከተቀበልክበት ከግብጽ ምድር የወጣህበትን ቀን ታስታውሳለህ።

4 እስከ ሰባት ቀን ድረስ በምድርህ በማንኛውም ሰው ቤት እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ቀን ማታ ለመሥዋዕት የታረደው እንስሳ ሥጋው በሙሉ በዚያው ሌሊት ተበልቶ ማለቅ አለበት።

5 “ለፋሲካ የተመደበውንም እንስሳ ማረድ የሚገባህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር በማንኛውም ከተማ አይደለም።

6 ነገር ግን የመሥዋዕቱን እንስሳ የምታርደው እግዚአብሔር አምላክህ ለስሙ መጠሪያ በመረጠው ስፍራ ብቻ ነው። ይኸውም ፀሐይ ስትጠልቅ ከግብጽ በወጣህበት ቀን የወጣህበትን ሰዓት በመጠበቅ ነው።

7 ሥጋውን ቀቅለህ እግዚአብሔር አምላክህ በሚመርጠው ቦታ ብላው፤ በማግስቱ ወደ ድንኳኖችህ ተመለስ።

8 በሚከተሉት ስድስት ቀኖች ደግሞ እርሾ ሳይነካው የተዘጋጀ ቂጣ ትበላለህ፤ በሰባተኛው ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ትሰግድ ዘንድ ጉባኤ ይሁን፤ በዚያ ቀን ሥራ አትሥራበት።


የመከር በዓል
( ዘፀ. 34፥22 ፤ ዘሌ. 23፥15-21 )

9 “የእህል አጨዳ ከጀመርክበት ጊዜ አንሥቶ ሰባት ሳምንት ቊጠር፤

10 ከዚያም እግዚአብሔር አምላክህ በሰጠህ በረከት መጠን የበጎ ፈቃድ መሥዋዕትህን በማቅረብ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የመከር በዓል አድርግ።

11 ከወንዶችና ከሴቶች ልጆችህ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮችህ በከተሞችህ ከሚኖሩት ሌዋውያን፥ በአገርህ የሚኖሩ መጻተኞች፥ እናትና አባት ከሌላቸው ድኻ አደጎችና ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ሴቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት እርሱ ለስሙ መጠሪያ እንዲሆን በመረጠው ቦታ በአንድነት ተሰብስበህ ደስ ይበልህ።

12 እነዚህን ድንጋጌዎች በጥንቃቄ ጠብቅ፤ አንተም ቀድሞ በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርክ አስታውስ።


የዳስ በዓል
( ዘሌ. 23፥33-43 )

13 “የእህልህን መከር ከሰበሰብክና የወይን ፍሬህን ከጨመቅህ በኋላ እስከ ሰባት ቀን ድረስ የዳስ በዓል ታከብራለህ፤

14 እርሱንም ከወንዶችና ከሴቶች ልጆችህ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮችህ፥ በከተሞችህ ከሚኖሩት ሌዋውያን፥ በአገርህ ከሚኖሩ መጻተኞች፥ እናትና አባት ከሌላቸው ድኻ አደጎችና ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ሴቶች ጋር አብረህ በመሆን ተደሰት።

15 አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጠው ቦታ ለሰባት ቀን ለእርሱ በዓል ታደርጋለህ፤ እግዚአብሔር አምላክህ፥ በምርትህና በምታደርጋቸው ድርጊቶች ሁሉ ስለሚባርክህ በዓሉን በደስታ ታከብራለህ።

16 “በዓመት ሦስት ጊዜ ወንዶች ሁሉ የፋሲካን፥ የመከርንና የዳስ በዓልን ለማክበር እግዚአብሔር አምላክህ በሚመርጠው ቦታ ይሰብሰቡ፤ በዓሉን ለማክበር በሚወጡበት ጊዜ ባዶ እጃቸውን አይምጡ፤

17 እያንዳንዱም የሚያመጣው ስጦታ እግዚአብሔር በሰጠው በረከት መጠን ይሁን።


የትክክለኛ ፍርድ አሰጣጥ ሁኔታ

18 “አምላክህ እግዚአብሔር ለየነገድህ በሚሰጠው ምድር በእያንዳንዱ ከተማ ዳኞችና ሌሎችንም ባለሥልጣኖች ትሾማለህ፤ እነዚህም ሰዎች ለሕዝቡ ያለ አድልዎ መፍረድ ይገባቸዋል፤

19 ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህ አታድላ፤ አታታል፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዐይን ስለሚያሳውርና የተጣመመ ፍርድ ስለሚያሰጥ ጉቦ አትቀበል።

20 እግዚአብሔር የሚሰጥህን ምድር ወርሰህ በሕይወት መኖር ትችል ዘንድ ሁልጊዜ ቅንና ትክክለኛ ሁን።


የተከለከሉ አምልኮዎች

21 “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ በምትሠራበት አጠገብ የማምለኪያ ዐፀድ (ዛፍ) አትትከል።

22 ደግሞም አምላክህ እግዚአብሔር የሚጠላውን የማምለኪያ የድንጋይ ምሰሶ አታቁም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos