ዘፀአት 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ትክክለኛ ፍርድ 1 “ሐሰተኛ ወሬ አታሰራጭ፥ ሐሰተኛ ምስክር ለመሆንም ከኃጢአተኛ ጋር አትተባበር። 2 ክፉ ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጣመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። 3 በፍርዱ ጊዜ ለድሀው አታድላ። 4 የጠላትህን በሬ ወይም አህያ ጠፍቶ ብታገኘው ለእርሱ መልስለት። 5 የሚጠላህን ሰው አህያ ከሸክሙ በታች ወድቆ ብታየው አትተወው፥ ነገር ግን እንዲነሳ እርዳው። 6 በፍርዱ ጊዜ የድሀውን ፍርድ አታጥምም። 7 ከሐሰት ነገር ራቅ፤ ንጹሑንና ጻድቁን አትግደል፥ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና። 8 ጉቦን አትቀበል፤ ጉቦ የሚያዩ ሰዎችን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። 9 መጻተኛውን አትጨቁን፤ እናንተ ራሳችሁ በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ የመጻተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች ታውቃላችሁና። ሰባተኛው ዓመትና ሰባተኛው ቀን 10 “ስድስት ዓመት ምድርህን ዝራ፥ ምርትዋንም ሰብስብ፤ 11 በሰባተኛው ዓመት ግን ተዋት አሳርፋትም፤ የሕዝብህ ድሆች ይበሉታል፤ እነርሱ ያስቀሩትንም የሜዳ እንስሳ ይብላው። በወይንህና በወይራህም ላይ እንዲሁ አድርግ። 12 ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ እንዲያርፉ የባርያህ ልጅና መጻተኛውም ዕረፍት እንዲሆንላቸው በሰባተኛው ቀን ዕረፍ። 13 የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ ጠብቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፥ ከአፍህም አይሰማ። ዓመታዊ በዓላት 14 “በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታደርግልኛለህ። 15 የቂጣውን በዓል ጠብቅ፤ በተመደበው በአቢብ ወር ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ እንዳዘዝሁህ ትበላለህ፤ በዚህ ወር ከግብጽ ምድር ወጥታችኋልና፥ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ። 16 የመከር በዓል፥ በእርሻህ የዘራኸውን የፍሬህን በኵራት፥ ዓመቱም ሳያልቅ ፍሬህን ከእርሻ በምትሰበስብበት ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ። 17 በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ። 18 የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ ቂጣ ጋር አትሠዋ፤ የበዓሌም ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቆይ። 19 የመጀመሪያውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ ጌታ አምላክህ ቤት አምጣ፤ ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል። ቃል የተገባችላቸው ከንዓንን መውረስ 20 “በመንገድ እንዲጠብቅህ፥ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ እንዲያስገባህ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እልካለሁ። 21 በፊቱ ተጠንቀቅ፥ ቃሉንም አድምጥ፤ ስሜ በእርሱ ስለ ሆነ ብትተላለፉ ይቅር አይልምና አታስመርረው። 22 አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጠላለሁ፥ የሚቃወሙህንም እቃወማለሁ። 23 መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ኬጢያውያን፥ ወደ ፌርዛውያን፥ ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ ኤዊያውያንና ወደ እያቡሳውያን ያገባሃል፤ እኔም አጠፋቸዋለሁ። 24 ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፥ አታገልግላቸውም፥ እንደ ሥራቸውም አትሥራ፤ ነገር ግን ፈጽመህ አፍርሳቸው፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብራቸው። 25 ጌታ አምላካችሁን ታገለግላላችሁ፤ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ። 26 በምድርህ የምትጨነግፍ ወይም መካን አትኖርም፤ የዘመንህን ቍጥር እሞላለሁ። 27 መፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፥ የምትሄድበትን ሕዝብ ሁሉ አስደንግጣቸዋለሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ በፊትህ ጀርባቸውን እንዲያዞሩ አደርጋለሁ። 28 በፊትህም ተርብ እሰድዳለሁ፥ ኤዊያዊውንም ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ከፊትህ አባርራለሁ። 29 ምድሪቱ ባድማ እንዳትሆን፥ የምድር አራዊትም እንዳይበዙብህ፥ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፊትህ አላባርራቸውም። 30 እስክትበዛና ምድርንም እስክትወርስ ድረስ በጥቂት በጥቂት አባርራቸዋለሁ። 31 ድንበርህንም ከቀይ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረበዳ እስከ ወንዙ ድረስ አደርጋለሁ፤ በምድሪቱ የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁና፥ ከፊትህ ታባርራቸዋለህ። 32 ከእነርሱ ጋርና ከአማልክቶቻቸው ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ። 33 በምድርህ አይቀመጡ አማልክቶቻቸውን በማገልገል እኔን እንድትበድል ያደርጉሃልና፥ ይህም ለአንተ ወጥመድ ይሆንብሃል።” |