1 ቆሮንቶስ 4:5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ስለዚህም፥ በጨለማ የተሰወረውን ወደ ብርሃን የሚያወጣ ደግሞም የልብን ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ፥ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም እያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ በምንም ነገር አትፍረዱ፤ ጌታ እስኪመጣ ጠብቁ። እርሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያመጣዋል፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውንም ሐሳብ ይገልጠዋል። በዚያ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ፥ ጌታ ለፍርድ ከመምጣቱ በፊት በማንም ላይ አትፍረዱ፤ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ በጨለማ የተሰወረውን ምሥጢር ወደ ብርሃን ያወጣዋል፤ በሰዎች ልብ የተደበቀውን ሐሳብ ይገልጠዋል፤ በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ተገቢውን ምስጋና ያገኛል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ጊዜው ሳይደርስ ዛሬ ለምን ትመረምራላቸሁ? በጨለማ ውስጥ የተሰወረውንም የሚያበራ፥ የልብን አሳብም የሚገልጥ ጌታችን ይመጣል፤ ያንጊዜ ሁሉም ዋጋውን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። |
አንተ ጐበዝ፥ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፥ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፥ በልብህም መንገድ ዐይኖችህም በሚያዩት ሂድ፥ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ።
የተመረጠውን መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ ጌታ ግን በእነርሱ ደስ አይሰኝም፤ በደላቸውን አሁን ያስታውሳል፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ።
በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ነገዶች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤
ስለዚህ “ያ ደቀመዝሙር አይሞትም” የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰማ፤ ነገር ግን ኢየሱስ “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ ምን ግድ አለህ?” አለው እንጂ “አይሞትም፤” አላለውም ነበር።
ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሆይ! የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው ላይ በምትፈርድበት ነገር በራስህ ላይ ትፈርዳለህ፤ ፈራጅ የሆንከው አንተ ያንኑ ታደርጋለህና።
ነገር ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፤ መገረዝም በመንፈስ የሆነ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በፊደል አይደለም፤ ምስጋናውም ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።
የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናል፤ በተንኮል አንመላለስም ወይም የእግዚአብሔርን ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናቀርባለን።
ወንድሞች ሆይ! እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፥ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ።
በዚህም በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ ነው።
እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት የምትጠባበቁ የምታፋጥኑ ሁኑ፤ ምክንያቱም ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የፍጥረት መሰረተ ነገር በእሳት ግለት ይቀልጣሉ!
እነርሱም “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ፥ የቀድሞ አባቶቻችን ከሞቱበት ጊዜ አንሥቶ፥ ሁሉ እንዳለ ይኖራል” ይላሉ።
ሙታንን፥ እንዲሁም ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላም መጽሐፍ ተከፈተ፤ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት በተጻፈው መሠረት፥ እንደ ሥራቸው መጠን ፍርድን ተቀበሉ።