1 ቆሮንቶስ 15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የክርስቶስ ትንሣኤ 1 ወንድሞች ሆይ! አሁን የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ 2 የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፥ ያመናችሁት በከንቱ ካልሆነ በስተቀር፥ የምትድኑበትን ወንጌል ነው። 3 እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ለኀጢአታችን ሞተ፤ 4 ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ 5 ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ 6 ከዚያም በኋላም ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ እስካሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። 7 ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፤ 8 ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር ለእኔ ደግሞ ታየ። 9 እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ፥ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ እንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን አሳድጃለሁ፤ 10 ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ ይልቁን ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ሆኖም ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። 11 እንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው። የሙታን ትንሣኤ 12 ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፥ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? 13 የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነው። 14 ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። 15 ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፥ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፥ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ 16 ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፥ ክርስቶስም አልተነሣም። 17 ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። 18 በክርስቶስም ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። 19 ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። 20 ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በእርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። 21 ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደመጣ፥ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። 22 ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፥ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ 23 ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፥ በኋላም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የእርሱ የሆኑት። 24 ከዚያም ግዛትን፥ ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፥ ያንጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። 25 ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። 26 የሚደመሰሰው የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ 27 “ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሏልና፤ ነገር ግን፥ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፥ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። 28 ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል። 29 ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? 30 እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? 31 ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክህት አረጋግጣለሁ። 32 እንደ ሰው አስተሳሰብ በኤፌሶን ከአራዊት ጋር መታገሌ ምን ሊፈይድልኝ ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፤ ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 33 አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” 34 ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና ይህንንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው። የትንሣኤ አካል 35 ነገር ግን አንዱ፥ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚወጡትስ በምን ዓይነት አካል ነው?” ብሎ ቢጠይቅ። 36 አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። 37 የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዘር ቅንጣት እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። 38 እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዓይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። 39 ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንሰሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዓይነት ነው። 40 እንዲሁም ሰማያውያን አካሎች አሉ፤ ምድራውያን አካሎች አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካሎች ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካሎች ክብር ሌላ ነው። 41 የፀሓይ ክብር አንድ ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው፤ የከዋክብት ደግሞ ሌላ ነው፤ የአንዱም ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል። 42 የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ 43 በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ 44 አካላዊ ሰውነት ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። አካላዊ ሰውነት አለ፤ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። 45 ስለዚህ፥ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። 46 ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን አካላዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። 47 የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። 48 ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። 49 የምድራዊውን ሰው መልክ እንደለበስን፥ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። 50 ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። 51 እነሆ፥ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ! ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ 52 የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፥ ድንገት፥ በቅጽበተ ዐይን፥ መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። 53 የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። 54 የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፥ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። 55 “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መውጊያህስ የት አለ?”። 56 የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው። 57 ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 58 ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ድካማችሁ በጌታ ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር በማወቅ፥ ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ። |