1 ተሰሎንቄ 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ 2 የጌታ ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ የሚመጣ መሆኑን እናንተው ራሳችሁ በጥንቃቄ አውቃችኋልና። 3 እነርሱም፦ “ሰላምና ደኅንነት ነው” በሚሉ ጊዜ ምጥ እንደ ያዛት እርጉዝ ሴት ድንገተኛ ጥፋት በእነርሱ ላይ ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም። 4 ወንድሞች ሆይ! እናንተ ግን ቀኑ እንደ ሌባ እንዳይመጣባችሁ በጨለማ ውስጥ አይደላችሁም፤ 5 እናንተ ሁላችሁም የብርሃን ልጆች፥ የቀንም ልጆች ናችሁና፤ ሆኖም እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም። 6 እንግዲያስ እንንቃ፥ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ። 7 የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፤ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤ 8 እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን በመጠን እንኑር፤ የእምነትንና የፍቅርንም ጥሩር፥ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንልበስ፤ 9 እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳንን እንድናገኝ እንጂ ለቁጣ እንድንሆን አስቀድሞ አልመረጠንም። 10 የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንድንኖር ስለ እኛ ሞተ። 11 ስለዚህ እናንተ በእርግጥ እያደረጋችሁት እንዳላችሁት፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ አንዱም ሌላውን ያንጸው። የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ 12 ወንድሞች ሆይ! በእናንተ መካከል የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም እንድታውቁ፥ 13 ስለ ሥራቸውም በፍቅር እጅግ እንድታከብሩአቸው እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ። 14 ወንድሞች ሆይ! እንመክራችኋለን፤ ሰነፎችን ገሥጹ፤ ፈሪዎችን አጽኑ፤ ደካሞችን እርዱ፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ። 15 ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ እንዲሁም ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ። 16 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ 17 ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ 18 በሁሉ ነገር አመስግኑ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ይህ ነውና። 19 መንፈስን አታዳፍኑ፤ 20 ትንቢትን አትናቁ፤ 21 ነገር ግን ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካሙንም አጥብቃችሁ ያዙ፤ 22 ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ። 23 የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። 24 የሚጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል። 25 ወንድሞች ሆይ! ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ። 26 ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። 27 ይህ መልእክት ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ ዐደራ እላችኋለሁ። 28 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። |