ለድሆችና ለችግረኞች መደረግ ስለሚገባው1 ልጄ ሆይ፥ ድሃውን የሚኖርበትን አትከልክለው፤ ከሚለምንህም ዐይኖችህን አትመልስ። 2 የተራበች ሰውነትን አታሳዝን፥ ያዘነ ሰውንም አታበሳጭ። 3 ያዘነ ልቡናን አታስደንግጥ፤ የሚለምንህንም አትለፈው። 4 በሚያገለግልህም ቤተ ሰብህ ላይ አትቈጣ፤ ከድሃም ፊትህን አትመልስ። 5 ከሚለምንህም ዐይንህን አትመልስ፤ ይረግምህም ዘንድ ለሰው ምክንያት አትስጠው፤ 6 በልቡናው አዝኖ ቢረግምህ ፈጣሪው ጸሎቱን ይሰማዋልና። 7 በብዙ ሰዎች ዘንድ እንድትወደድ ሁን፤ በዳኞች ዘንድ አገልግል፤ ራስህንም ከፍ ከፍ አታድርግ። 8 ድሃውን በጆሮህ አድምጠው፤ በየዋህነትም በጎ ቃልን መልስለት። 9 የተበደለውንም ሰው ከሚበድለው ሰው እጅ አድነው፤ ለእርሱም መፍረድን ቸል አትበል። 10 አባቱ ለሞተበት ልጅ እንደ አባት ሁነው፤ ለእናቱም እንደ ባሏ ቁምላት፤ እንደ ልዑልም ልጆች ትሆናለህ፥ ከእናትህም ይልቅ ይወድሃል። ጥበብ ከፍ ከፍ እንደምታደርግ11 ጥበብስ ልጆችዋን ከፍ ከፍ አደረገቻቸው፤ የሚፈልጓትንም ትቀበላቸዋለች። 12 እርሷን የወደደ ሕይወቱን ወደደ፤ ወደ እርሷም የሚገሠግሥ ሰው በደስታ ይሞላል። 13 አጥንቶ የሚይዛት ሰውም ክብርን ይወርሳል፥ እርስዋም ያደረችበትን እግዚአብሔር ይባርካል። 14 እርስዋንም የሚያገለግሉ ቅዱሱን ያገለግላሉ፤ የሚወዱኣትንም እግዚአብሔር ይወዳቸዋል። 15 እርስዋን የሚሰማትም አሕዛብን ይገዛል፤ እርስዋንም የሚያደምጣት ሰው ተዘልሎ ይኖራል። 16 ካመንኻት ታገኛታለህ፤ በዘመንህም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች። 17 ከእርሱ ጋር ትሄድ ዘንድ ትቀድማለች፤ ፈጽማም ታስፈራዋለች፥ ሰውነቱን እስክታስገዛና በተግሣጽዋ እስክትፈትነው ድረስ፥ ትገርፈዋለች ታስተምረዋለችም። 18 ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ተቀብላ ደስ ታሰኘዋለች፤ ምሥጢርዋንም ትገልጥለታለች። 19 ከእርሷ ወጥቶ ቢስት ግን ትለየዋለች። በጠላቱም እጅ ትጥለዋለች። 20 ጊዜውን ጠብቅ፥ ከክፉ ነገርም ተጠንቀቅ፤ ስለ ነፍስህ በማፈር አታድላ። 21 በማፈር ኀጢአትን የሚሠራ አለና፤ በማፈርም ጽድቅን የሚሠራ ሞገስንም የሚያገኝ አለና። 22 ጕዳት በራስህ ስለሚደርስብህ የሰው ፊት አይተህ አታድላ፥ ሰውነትህን እንዳትጥል አትፈር። 23 የሚናገርን ሰው መናገሩን አትከልክለው፤ ከቃሉ የተነሣ ጥበቡ ይታወቃልና፥ ትምህርቱም ከአንደበቱ ንግግር የተነሣ ይታወቃልና። 24 ጽድቅን አትቃወም። ስለ በደልኸውም በደል ንስሓ ግባ። 25 ኀጢአትህንም መናገር አትፈር፥ የውኃ ሙላትን አትደፋፈር። 26 ለሰነፍ ሰው ራስህን አታዋርድ፤ ለታላቅ ሰው ፊትም አታድላ። 27 ፈጣሪህ እግዚአብሔር ስለ አንተ ይከራከርልሃልና ለሞት እስክትደርስ ስለ እውነት ተከራከር። 28 በአፍህ አውታታ አትሁን፤ ሥራህንም ቸል አትበል። 29 በቤትህ እንደ አንበሳ አስፈሪ አትሁን፤ ቤተ ሰብህንም አታስደንግጥ፤ 30 ለመበደር እጅህን አትዘርጋ። በመክፈልም ጊዜ እጅህን ለመሰብሰብ አትመለስ። |