1 እርሱም ታናናሽ ልጆቹን ትቶ ሞተ፤ አባታቸውም ሥርዐት እንደ ሠራላቸው አደጉ፤ የቤታቸውንም ሥርዐት ጠበቁ፤ ወገናቸውንም ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ድሃውንና ባልቴቶችን፥ የሙት ልጆችንም አያስጮሁም ነበር። 2 እግዚአብሔርንም ይፈሩት ነበር፤ ገንዘባቸውንም ለድሆች ይመጸውቱ ነበር፤ አባታቸውም አደራ ያላቸውን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ባልቴትዋንና የሙት ልጆችንም በችጋራቸው ጊዜ ያረጋጓቸው ነበር፤ አባትና እናትም ይሆኗቸው ነበር፤ ከሚበድሏቸው ሰዎች እጅ ያስጥሏቸው፥ ካገኛቸው ሁከትና ኀዘንም ሁሉ ያረጋጓቸው ነበር። 3 እንዲህም እያደረጉ አምስት ዓመት ኖሩ። 4 ከዚህም በኋላ የከለዳውያን ንጉሥ ጺሩጻይዳን መጣ፤ ሀገራቸውንም ሁሉ አጠፋ፤ የመቃቢስንም ልጆች ማረካቸው፤ መንደራቸውንም ሁሉ አጠፋ። 5 ገንዘባቸውንም ሁሉ ዘረፈ፤ እነርሱንም በእግዚአብሔር ትእዛዝና ፍርድ የማይሔዱ፥ ነገር ግን በክፋት ሁሉና በዝሙት፥ በርኵሰትና በስስት፥ በፅርፈትና አምላካቸውን ባለማሰብ የሚሔዱ ጣዖት አምላኪዎች ይዘው ወደ ሀገራቸው ወሰዷቸው። 6 የሞተውንና ደሙን፥ አውሬ የበላውንና የበከተውን፥ እግዚአብሔርም የማይወድደውን ሁሉ ይበላሉ፤ በኦሪት ከተጻፈው ከእውነተኛው ትእዛዝም ሁሉ ሕግ የላቸውም። 7 እግዚአብሔርንም ከእናታቸው ማኅፀን ያወጣቸውና በሚገባ የመገባቸው፥ ፈጣሪያቸውና መድኀኒታቸውም እንደ ሆነ አያውቁትም። 8 በፍርድ ጊዜም ሕግ የላቸውም፤ የእንጀራ እናታቸውንና አክስታቸውን አግብተው ወደ ቅሚያና ወደ ክፉ ነገር፥ ወደ ኀጢአትና ወደ ዝሙትም ይሄዳሉ እንጂ። ክፉውንም ሁሉ ያደርጋሉ፤ እኅቶቻቸውንና ዘመዶቻቸውንም ያገባሉ፤ ሕግም የላቸውም። 9 መንገዳቸውም ሁሉ ድጥና ጨለማ፤ ርኵሰትና ዝሙት ነው። 10 እነዚያ የመቃቢስ ልጆች ግን በሥርዐታቸው ሁሉ ይጠበቁ ነበር፤ ሞቶ ያደረውንና አባላ የተመታውን አይበሉም ነበር፤ የከለዳውያንንም ልጆች ርኵሰትና ኀጢአታቸውን ሁሉ አይሠሩም ነበር። በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ የኃጥኣንና የወንጀለኞች፥ የመናፍቃንና የከዳተኞች፥ ፍጹም ርኩሰትንና ቅሚያን የተሞሉ የአረማውያን ልጆች የሚሠሩት ሥራቸው ክፉና ብዙ ነበርና። 11 ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር የሚወድደው ሥራ ሁሉ በእነርሱ ዘንድ አልነበረም። 12 ዳግመኛም ስሙ ብኤል ፌጎር የሚባል ጣዖትን ያመልኩ ነበር፤ እንደ ፈጣሪያቸው እንደ እግዚአብሔርም ያመልኩትና ይታመኑት ነበር። እርሱ ግን ደንቆሮና ዲዳ ስለሆነ የሚያየውና የሚሰማው የለም፤ የሰው እጅ ሥራ ጣዖት ነውና፤ ብርና ወርቅን የሚሠራ አንጥረኛ የሠራው፥ ትንፋሽና ዕውቀት የሌለው የሰው እጅ ሥራ ነው፤ 13 አይበላም፤ አይጠጣምም። 14 አይገድልም፦ አያድንምም። 15 አይተክልም፦ አይነቅልምም። 16 መልካም አያደርግም፤ ክፉም አያደርግም። 17 አያደኸይም፦ አያከብርምም። 18 አይቀሥፍም፤ ይቅርም አይልም። ነገር ግን ሰነፎች የከለዳውያንን ሕዝብ ለማሳት ዕንቅፋትን ይሆናል። |