ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በኢያሱም እነርሱን ያዳነበት ጊዜ አለ። 2 በጌዴዎን እነርሱን ያዳነበት ጊዜ አለ። 3 በሶምሶን፥ በባርቅና በዲቦራ፥ በዮዲትም እነርሱን ያዳነበት ጊዜ አለ፤ በሴትም ቢሆን፥ በወንድም ቢሆን አድሮ ከሚያሠቃዩአቸው ጠላቶቻቸው እጅ ያድኗቸው ዘንድ መሳፍንትን ያስነሣላቸው ነበር። 4 እግዚአብሔርም እንደ ወደደ ከሚያሠቃዩአቸው ሰዎች እጅ ያድናቸው ነበር። 5 በአደረገላቸውም በጎ ነገር ሁሉ በምድራቸው ዘር፥ በምድረ በዳ ያለ መንጋቸውን ሁሉና ከብታቸውንም በማብዛት ደስ ይላቸው ነበር። 6 ከብታቸውንና ተክላቸውን ይባርክላቸው ነበር፤ በቤትና በምድረ በዳ የያዙትንም ሁሉ ይባርክላቸው ነበር፤ በዐይነ ምሕረት ይመለከታቸው ነበርና እንስሶቻቸውን አያሳንስባቸውም ነበር፤ የጻድቃን ልጆች ናቸውና ፈጽሞ ይወዳቸው ነበር። 7 እነርሱ ግን በሥራቸው ክፉ በሆኑ ጊዜ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። 8 በሚያጠፋቸውም ጊዜ ወዲያውኑ ይሹት ነበር፤ ተመልሰውም ወደ ፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔር ይገሠግሡ ነበር። 9 በፍጹም ልቡናቸውም በተመለሱ ጊዜ ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸው ነበር፤ ሥጋና ደም እንደ ሆኑ ያውቃቸዋልና የሚያስት የዚህ ዓለም አሳብና፥ አጋንንትም አሉባቸውና የቀደመ ኀጢአታቸውን አያስብባቸውም ነበር። 10 ያ መቃቢስ ግን እግዚአብሔር በቅዱሱ ተራራ የሠራውን ይህን ሥርዐት በሰማ ጊዜ በንስሓ ተጋደለ። 11 ይኸን ነገር ከአየና ከሰማ በኋላም በጎ ሥራ መሥራትን አላቃለለም፤ እግዚአብሔር ይቅር ብሎአቸዋልና የእስራኤል ልጆች የሚሠሩትን ቸርነት ሁሉ መሥራት አላቃለለም፤ ትእዛዙንም ሲተላለፉ እግዚአብሔር በሚቀሥፋቸው ጊዜ ያለቅሱና ይጮሁ ነበር፤ ዳግመኛም ይቅር ይላቸው ነበር፤ ሕጉንም ይጠብቁት ነበር። 12 መቃቢስም እንደዚሁ መንገዱን ያቀና ነበር፤ ትእዛዙንም ይጠብቅ ነበር፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ትእዛዝም ይሔድ ነበር። 13 ያንጊዜም የእስራኤል ልጆች የሚመኩበትን ሁሉ ከሰማ በኋላ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቅ እንደ እነርሱ ይመካ ነበር። 14 ቤቱንና ልጆቹንም በእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ ሁሉ ይሄዱ ዘንድ ይሠራራ ነበር። 15 አይሁድ የሚከለከሉትን ሥርዐት እርሱም ይከለከል ነበር፤ አይሁድም የሚጠብቁትን ትእዛዝ ሰምቶ ይጠብቅ ነበር፤ እርሱ ልዩ ሞዓባዊ ወገን ሲሆን አይሁድ የሚከለከሉትን ምግብም ይከለከል ነበር። 16 ዐሥራትም ያወጣ ነበር፤ ከበጎቹና ከላሞቹ፥ ከአህዮቹም መጀመሪያ የተወለደውንና የገዛውን ሁሉ ይሰጥ ነበር፤ እንዲሁም አይሁድ የሚሠዉትን መሥዋዕት ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ ይሠዋ ነበር። 17 የስእለቱንና የኀጢአቱን፥ የፈቃዱንና የሰላሙን መሥዋዕትና የዘወትሩን መሥዋዕት ይሠዋ ነበር። 18 የአዝመራውንም መጀመሪያ ይሰጥ ነበር፤ አይሁድም የሚያቀርቡትን የወይኑን ቍርባን ያቀርብና ለሾመው ለሌዋዊው ይሰጥ ነበር፤ አይሁድም የሚያደርጉትን ሁሉ እንዲሁ ያደርግ ነበር፤ ዕጣኑንም ያጣፍጥ ነበር። 19 መቅረዝንና ጋኖችን፥ ጠረጴዛዎችንና ድንኳኖችን፥ አራቱን ኅብርና ቀለበቶችን፥ ለቅድስተ ቅዱሳኑም መብራት የተጣራ ዘይትን፥ እግዚአብሔርን በሚያገለግሉበት ጊዜ እስራኤል በቅድስተ ቅዱሳኑ እንደሚያደርጉት መጋረጃን አሠራ። 20 በሕጉና በሥርዐቱ በኖሩ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ቸል ብሎ በጠላቶቻቸው እጅ ባልጣላቸው ጊዜ፥ መቃቢስም እንደ እነርሱ በመንገዱ ሁሉ በጎ ሥራ ይሠራ ነበር። 21 መሪ እንዲሆነው፥ ከመረጣቸውና ፈቃዱን ከአደረጉ ከእስራኤል ወገኖችም እንዳይለየው ሁልጊዜ ወደ እስራኤል ፈጣሪ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር። 22 በጽዮን ልጅን፥ በኢየሩሳሌምም ቤትን ይሰጠው ዘንድ፥ በነቢዩ አንደበት ከተናገረው ከጥፋትም ያድነው ዘንድ ንስሓ በገባበትና በእግዚአብሔር ፊት በአለቀሰው ልቅሶ ሁሉ ንስሓውን ይቀበለው ዘንድ፥ 23 ዘሩንም ከምድር እንዳያጠፋበት፥ በመግባቱና በመውጣቱም ይጠብቀው ዘንድ ዳግመኛ ይጸልይ ነበር። 24 በመቃቢስ ሥልጣን በታች ከአሉ ከሞዓብ አሕዛብም ያምኑ ዘንድ ደስ አላቸው፤ አለቃቸው በቀናች መንገድ ይሄድ ነበርና፥ ፍርዱንም ይመለከቱ ነበር፤ ፈቃዱንም ያደርጉ ነበር፤ የአገራቸውን ፍርድና ያገራቸውን ቋንቋ ይንቁ ነበርና የመቃቢስም ሥራ እንደሚቀናና እንደሚሻል ያስተውሉ ነበር። 25 ወደ እርሱም መጥተው የመቃቢስን የቸርነቱንና የእውነቱን ፍርድ ይሰሙ ነበር። 26 ብዙ ገንዘብም ነበረው፤ ወንዶች ባሮችና ሴቶች ባሮች፥ ግመሎችና አህዮችም ነበሩት፤ ጥሩር የሚለብሱ አምስት መቶ ፈረሶችም ነበሩት፤ ኢሎፍላውያንንና አማሌቃውያንን፥ ሶርያውያንንም ፈጽሞ ድል ይነሣቸው ነበር፤ ቀድሞ ጣዖት ሲያመልክ ግን ድል ሲነሡት ኖረ። 27 እግዚአብሔርን ከአመነ ወዲህ ግን ወደ ሰልፍ ሲሄድ እርሱ ድል ይነሣ ነበር እንጂ እርሱን ድል የነሣው አልነበረም። 28 እነርሱ ግን ይወጉት ዘንድ በጣዖቶቻቸው ኀይል ይመጡ ነበር፤ በጣዖቶቻቸውም ስም ጠርተው ይረግሙት ነበር፤ ነገር ግን እምነቱን በፈጣሪው በእግዚአብሔር ላይ አድርጓልና ድል የሚነሣው አልነበረም። 29 እንዲህም እያደረገና ጠላቶቹንም ድል እየነሣ፥ አሕዛብንም በሥልጣኑ እየገዛ ኖረ። 30 ስለ ተበደሉትም ይበቀል ነበር፤ የድሃአደጉንም ፍርድ ያጸድቅ ነበር፤ 31 ባልቴቶችንና ድሃአደጎችንም በችግራቸው ጊዜ ይቀበላቸው ነበር፤ የተራቡትንም ከምግብ ያጠግባቸው ነበር፤ የተራቈቱትንም ከልብሱ ያለብሳቸው ነበር። 32 በጥበቡና በእጁም ሥራ ደስ ይለው ነበር፤ ከአለውም ሳይነፍግ ይሰጥ ነበር፤ ለቤተ መቅደስም ዐሥራትን ይሰጥ ነበር፤ መቃቢስም ይኽን እያደረገ ሳለ በመልካም ዐረፈ። |