Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በሰማይም ያለ ቢሆን፥ በምድርም ያለ ቢሆን፥ ረቂቅም ቢሆን፥ ግዙፍም ቢሆን ሁሉም የእርሱ ነው፤ ሁሉም በሥርዐቱ ጸንቶ ይኖራል። 2 ከዓለሙ ሁሉ ፈጣሪ ሕግና ትእዛዝ የሚተላለፍ የለም፤ በሰማይ የሚበር የንስር ፍለጋ ቢሆን፥ ወደ ወደደበት መሄጃውን እርሱ ያዝዛል። 3 የእባብንም ጎዳና በዓለት ውስጥ እርሱ ወደ ወደደበት ያዝዛል፤ የመርከብንም ጎዳና በባሕር ውስጥ ከእግዚአብሔር ብቻ በቀር ጎዳናውን የሚያውቀው የለም። 4 የጻድቅም ነፍስ፥ የኃጥእም ነፍስ ብትሆን፥ ከሥጋዋ ከተለየች በኋላ ከእግዚአብሔር ብቻ በቀር ነፍስ የምትሄድበትን ጎዳና የሚያውቅ የለም። 5 በምድረ በዳ ወይም በተራራም ትዞር እንደ ሆነ የምትዞርበትን ማን ያውቃል? እንደ ወፍም ትበር እንደ ሆነ፥ በተራራውም ንቃቃት ላይ እንደሚወርድ እንደ አርሞንኤም ጠል ትሆን እንደ ሆነ፥ 6 እንደ ጥቅል ነፋስም ትሆን እንደ ሆነ፥ ጎዳናውን እንደሚያቀና መብረቅም ትሆን እንደ ሆነ፥ 7 በጥልቁ ላይም እንደሚያበሩ ከዋክብት ትሆን እንደ ሆነ፥ በጥልቁ መካከል እንደሚከመር እንደ ባሕር ዳር አሸዋም ትሆን እንደ ሆነ፥ 8 በባሕሩም ጥልቅ ዳርቻ እንደ ጸና እንደ አድማስ ድንጋይም ትሆን እንደ ሆነ፥ በውኃ መፍሰሻ እንደ በቀለች፥ የአማረ ፍሬዋንም እንደምትሰጥ ዛፍ ትሆን እንደ ሆነ፥ 9 ዋዕየ ፀሐይ እንደሚያቃጥለው፥ ነፋስም አንሥቶ ወደ አልበቀለበት ወደ ሌላ ቦታ እንደሚወስደው፥ ፍለጋውም እንደማይገኝ እንደ መቃ ትሆን እንደ ሆነ፥ ፍለጋው እንደማይገኝ እንደ ጉም ሽንትም ትሆን እንደ ሆነ ማን ያውቃል? 10 የእግዚአብሔርንስ መንገድ ማን ያውቃል? መካሮቹስ እነማን ናቸው? ከማንስ ጋር መከረ? 11 የእግዚአብሔር አሳቡ ከሰው የተሰወረ ነውና ፍለጋውን ማን ይከተላል? 12 የእግዚአብሔርን ምክሩንና ጥበቡን መመርመር የሚችል ማን ነው? እርሱ ምድርን በውኃ ላይ መሥርትዋታልና፥ ያለካስማም አጽንትዋታልና፥ በፍጹም ጥበቡም ሰማይን በነፋስ አጸናው፤ ተባዕታዊውንም ውኃ እንደ ድንኳን ዘረጋው። 13 ደመናትንም በምድር ላይ ዝናምን ያዘንሙ ዘንድ አዘዛቸው፤ ሣርንም ያበቅላል፤ በእግዚአብሔርም በአንድነት ደስ ይለን ዘንድ ለሰው ምግብ ሊሆኑ ቍጥር የሌላቸው ፍሬዎችን ያበቅላል። 14 እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በረከቱን ሁሉ፥ ደስታውንና ጥጋቡንም ይሰጣቸዋል ይኸውም ጠግበው ከምድር ፍሬ የሰጣቸውን እግዚአብሔርን ያመሰግኑት ዘንድ ነው። 15 የአማረ መጐናጸፊያንም ያለበሳቸውን፥ የሚፈለገውንም በረከት ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለሚፈጽሙ ሰዎች የተሰጠ ደስታውንና ተድላውንም ይሰጣቸዋል። 16 የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ለሚጠብቁ፥ ለአባቶቻቸው በአዘጋጀው ማደሪያ በሰማያት ክብርንና መወደድን ደስታንም ይሰጣቸዋል። 17 በአምልኮቱና በፍርዱ ለኖሩ፥ ሕጉን ይጠብቁ ዘንድ፥ ሥርዐቱንም ይሹ ዘንድ ለጠበቃቸውና ለመገባቸው፥ ለአሳደጋቸውና ለአከበራቸው፥ ከእርሱም ትእዛዝ ላልወጡ ክብርንና ሞገስን ይሰጣቸዋል፤ እኔም ጠላቶቻቸውን በማድከም፥ ሰውነታቸውንም በመጠበቅ እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ለወዳጆቹ የሚያደርገውን አየሁ። 18 ሁሉንም እንደ ለመኑት ይሰጣቸዋል፥ ፈቃዳቸውንም ይፈጽምላቸዋል፤ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ አትውጡ፤ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ፈጽሙ። 19 እንዳይቈጣባችሁ፥ በአንድ ጊዜም እንዳያጠፋችሁ፥ በቍጣውም እንዳይገርፋችሁ፥ ቀድሞ ከነበራችሁበት ከአባቶቻችሁ ርስትም እንዳትወጡ፥ ማደሪያችሁም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ መውጫ በሌለበት በገሃነም እንዳይሆን ከትእዛዙና ከሕጉ አትውጡ። 20 በእግዚአብሔር ፊት በቆማችሁ ጊዜ ሥራችሁ በጎ ይሆን ዘንድ ነፍሳችሁ ከሥጋችሁ ሳትለይ የፈጣሪያችሁን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠብቁ። 21 የሰማይና የምድር መንግሥት ለእርሱ ብቻ ነውና፤ ከሃሊነትም፥ መንግሥትም ለእርሱ ነውና፤ መራራትና ይቅር ማለትም ለእርሱ ብቻ ነው። 22 እርሱ ባለጸጋ ያደርጋልና፤ ያደኸያልምና፥ ያዋርዳልና፥ ያከብራልምና። 23 ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ብሎ ተናገረ፥ “ሰው ከንቱን ይመስላል፤ ዘመኑም እንደ ጥላ ያልፋል። 24 አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘለዓለም ትኖራለህ፤ ስም አጠራርህም ለልጅ ልጅ ነው።” 25 ዳግመኛም እንዲህ አለ፥ “መንግሥትህ የዘለዓለም መንግሥት ነው፤ አገዛዝህም ለልጅ ልጅ ነው፥” አንተ መንግሥትን ከሳኦል ወስደህ ለዳዊት ሰጠህ። 26 አንተን ግን የሚሾምህ የለም፤ አንተንም መሻር የሚችል የለም፤ አንተን ማየት የሚችል የለም፤ አንተ ግን ሁሉን ታያለህ። 27 መንግሥትህም ለልጅ ልጅ ዘመንና ለዘለዓለም አይሻርም፤ እርሱን የሚገዛው የለም፤ እርሱ ግን ሁሉን ይገዛል፤ ሁሉንም ያያል። 28 ያመሰግኑት ዘንድ ያለ ጥርጥርም በቀና ልቡና አምልኮቱን ያውቁ ዘንድ፥ ከፈጠራቸውና ከመገባቸው፥ ከአከበራቸውና ከአሳደጋቸው ከእግዚአብሔርም ብቻ በቀር ለሌሎች አማልክት የሚሰግዱ እንዳይሆኑ እርሱ ሰውን በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮታልና ልብንና ኵላሊትን ይመረምራል። 29 እነርሱ ግን የፈጠራቸውን እግዚአብሔርን ማምለክን እንቢ አሉ፤ ለድንጋይና ለእንጨት፥ የሰው እጅም ለሠራቸው ለብርና ለወርቅ ይሰግዳሉ። 30 በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ይቆም ዘንድ የመሥዋዕታቸው ጢስ ወደ ሰማይ እስኪወጣ ድረስ ይሠዉላቸዋል፤ ጣዖታቸውንም በማምለክ ሰለ ሠሩት ኀጢአታቸው ሁሉ ይከስሳቸዋል። 31 የተማሩትንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቁም። ነገር ግን ለጣዖት መስገድን፥ የሚገባ ያይደለ የጐደፈ ሥራንም ሁሉ፥ በኮከብ ማሟረትን፥ ጥንቆላንና ጣዖት ማምለክን፥ ክፉ ፈቃድንና እግዚአብሔር የማይወድደውንም ሥራ ሁሉ ተማሩ። 32 በእግዚአብሔርና በመላእክቱ ፊት እንዲመሰገኑ ከኀጢአትና ከበደል ሰውነታቸውን ያድኑ ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ማመስገንን አልወደዱምና በጎ ሥራ በማጣት ይኸን ሁሉ ይሠራሉ። 33 ከተቀበሩበትና አጥንቶቻቸው ከረገፉበት ከመቃብር ሁሉም በአንድነት በተነሡ ጊዜ፥ ነፍሳቸው በእግዚአብሔር ፊት ዕራቁትዋን ትቆማለች፤ ነፍሳቸውም ለደጋጎች ሰዎች በተዘጋጁ በብርሃን ቤቶች ትኖራለች። 34 የኀጢአተኞች ሰዎች ነፍስ ግን በጨለማ ትኖራለች፤ መቃብራትም በተከፈቱ ጊዜ ሥጋዎች ይነሣሉ፤ ነፍሳትም ቀድሞ ወደ ተለዩአቸው ሥጋዎች ይመለሳሉ። 35 ዕራቁታቸውን እንደ ተወለዱ በእግዚአብሔር ፊት ዕራቁታቸውን ይቆማሉ፤ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ እስከዚያ ጊዜ የሠሩት ኀጢአታቸውም ይገለጣል። 36 ኀጢአታቸውን በጫንቃቸው ይሸከማሉ፤ ጥቂትም ቢሆን፥ ብዙም ቢሆን፥ ኀጢአት ቢሠሩ እንደ ሠሩት ሥራቸው ይቀበላሉ። |