La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


መጽሐፈ ሲራክ 45 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
መጽሐፈ ሲራክ 45

ሙሴ

1 ከያዕቆብ ዘር አንድ ደግ ሰው ፈጠረ፤ እርሱም በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አገኘ፤ በእግዚአብሔርና በሰዎች ዘንድ የተወደደው፥ የሙሴ መታሰቢያው የተባረከ ነው።

2 ከቅዱሳን ጋር የሚተካከል ክብር፥ ጠላቶቹንም የሚያሸብር ብርታት ሰጠው።

3 በሙሴ ቃል ድንቅ ነገሮችን ተወ፥ በነገሥታትም ፊት ከፍ ከፍ አደረገው። ሕዝቡ የሚፈጽሟቸውን ትእዛዛት ሰጠው። ከክብሩም በከፊል አሳየው።

4 በታማኝነቱና በደግነቱ ቀደሰው፤ ከሰዎችም ሁሉ መረጠው።

5 ድምፁን እንዲሰማ ፈቀደለ፥ ወደ ጨለማውም መራው።

6 ለያዕቆብ ሕጐቹን፥ ለእስራኤል አዋጆቹን ያስተምር ዘንድ፥ ትእዛዛቱን ፊት ለፊት ሰጠው።

አሮን

7 ከሌዌ ነገድ የሆነ ወንድሙን፥ እንደ እርሱ የተቀደሰውን አሮንን አስነሣ። ከእርሱም ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አደረገ፥ ሕዝቡን እንዲያገለግልም ክህነትን ሰጠው። በልብሰ ተክህኖ አንቆጠቆጠው፤ የክብርም ካባ አጐናጸፈው።

8 ታላቅነትን አለበሰው፥ ውድ የሆኑ ጌጦች፥ ሱሪ፥ ቀሚስና ካባም ሸለመው።

9 በቀሚሱ ዙሪያ የሚደረግ የሮማን መርገፍ፥ እርሱ በተራመደ ቍጥር የሚያቃጭሉ፥ ቤተ መቅደሱን በድምፃቸው የሚሞሉ፥ የሕዝቦች ልጆች መታሰቢያ የሆኑ፥ የወርቅ ደውሎችንም ሰጠው።

10 በጌጥ የተሠራ የተቀደሰ የወርቅ ልብስ፥ በአዋቂ የተሠራ ወይን ጠጅ ከፋይ፥ ጠቢብ የሠራቸው የተጐነጐኑ የቀያይ የፍርድ ሜዳልያዎች፥

11 በወርቅ የተለበጡ ጠቢብ የሠራቸው፥ እንደ ማኀተም የተቀረጹ የክብሩ ደንጊያዎች፥ የእስራኤልን ነገዶች ቍጥር በውስጣቸው የያዙ መታሰቢያዎች፥

12 ለዐይን ደስ የሚያሰኝ የቅድስና ማኀተም የተቀረጸበት፥ እጅግ ያጌጠና የድንቅ ሥራ ውጤት የሆነ፥ በጥምጥሙ ላይ የሚያርፍ የወርቅ አክሊልም ሰጠው።

13 ከእርሱ በፊት ይህን የመሰለ ውብ ነገር ከቶ አልነበረም፥ ከእርሱም በኋለ ከልጆቹና ከወገኖቹ በቀር፥ ማንም ቢሆን ጨርሶ አልለበሳቸውም።

14 መሥዋዕቶቹም በቀን ሁለት ጊዜ የሚቀርቡ፥ የማይቋርጡና ሙሉ በሙሉም የሚቃጠሉ ነበሩ።

15 ሙሴ ቀደሰው፥ በቅዱሱም ዘይት ቀባው፥ ይህም ለእርሱና ለወገኖቹም ጭምር፥ እስከ ሕልፈተ ሰማይ የገባው ቃል ኪዳን ነው፥ የአምልኮውን ሥርዓት እንዲመራ፥ ካህን ሆኖም በእግዚአብሔር ስም ሕዝቡን እንዲባርክ ሥልጣን ሰጠው።

16 ለሕዝቡ ኃጢአት ስርየት ዕጣንና ሽቶን በመታሰቢያነት፥ መሥዋዕቶችንም ለጌታ ያቀርብ ዘንድ፥ ከነበሩት ሁሉ እርሱን መረጠው።

17 ያዕቆብን ያስተምር፥ እሥራኤልንም በሕጉ ያሰለጥን ዘንድ፥ ትእዘዙን ሰጠው፥ ሕጉንም አስረከበው።

18 ሌሎች ግን በእርሱ ላይ አሴሩ፥ በበረሃማ ሳሉ ተመቀኙት፥ ዳታን አቢሮንና ተከታዮቻቸው፥ ኮፊና ወገኖቹም ጭምር በቁጣ ተነስተውበታል።

19 ጌታ ይህን ባየ ጊዜ አዘነ፥ በቁጣው ቀሰፋቸው። በእነርሱ ላይ ተአምራቱን ሠራ በእሳትም ነበልባል ፈጃቸው።

20 የአሮንን ክብር ከፍ አደረገ፥ ውርስም ሰጠው፥ የመጀመሪያዎቹ ፍሬዎች የእርሱ ድርሻ እንዲሆኑ፥ ከሁሉም በፊት ያሻውን ያህል እንጀራ እንዲወስድም ፈቀደ።

21 እነርሱም ለእርሱና ለዘሮቹ የፈቀደላቸውን የጌታን መሥዋዕቶች ይመገባሉ።

22 ከሕዝቡ ርስት ግን አይካፈልም፥ ያንተ ድርሻና ርስት እኔ ነኝ ባለው መሠረት ከሕዝቡ መካከል ድርሻ የሌለው እርሱ ብቻ ነው።

ፊንሃስ

23 ጌታን በመፍራት ትጋቱ፥ ሕዝቡ ባመፀ ወቅት በእምነቱ በመጽናቱ፥ በልበ ሙሉነትና በድፍረት በመቆሙ፥ ለእሥራኤልም ስርየትን በማስገኘቱ፥ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስ ክብርን በተመለከተ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው።

24 ከዚህም የተነሣ፥ የቤተ መቅደሱና የሕዝቡ አለቃ ሆኖ ከመመረጡመ በላይ፥ እርሱና የእርሱ ወገኖች የክህነት እልቅናን ለዘለዓለምም ያገኙ ዘንድ ቃል ኪዳንን አገኙ።

25 ከይሁዳ ነገድ ከእሴይ ልጅ፥ ከዳዊትም ጋር እንዲሁ፥ ከልጅ ወደ ልጅ ብቻ የሚተላለፍ የዙፋን ውርስ፥ ቃል ኪዳን ነበር። የአሮን ውርስ ግን ለወገኖቹ ሁሉ ይተላለፋል።

26 የአባቶቻችሁ ደግነት እንዳይጠፋ፥ ወገኖቻቸውም ክብራቸውን እንዳወርሱ፥ ሕዝቡን በትክክል ታስተዳድሩ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ልባችሁን በጥበብ ይሙላው።