ሮሜ 1:20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኀይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፤ መልስ የሚሰጡበትን ምክንያት እንዳያገኙ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፣ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታዩት ነገሮች፥ ይኸውም ዘላለማዊው ኃይሉና መለኮታዊነቱ ታውቆ፥ ግልፅም ሆኖ ስለሚታይ ሰበብ የላቸውም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለሰዎች የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፥ ይኸውም ዘለዓለማዊው ኀይሉና አምላክነቱ እርሱ በፈጠራቸው ነገሮች አማካይነት ግልጥ ሆኖ ስለ ታየ ሰዎች ለሚያጠፉት ጥፋት ምክንያት የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። |
አብርሃምም በዐዘቅተ መሐላ አጠገብ የተምር ዛፍን ተከለ፤ በዚያም የዘለዓለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ።
ዐይናችሁን ወደ ሰማይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ ይህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? ከዋክብትንም በሙሉ የሚቈጥራቸው እርሱ ነው፤ በየጊዜያቸው ያመጣቸዋል፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በክብሩ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።
ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፤
ባልመጣሁና ባልነገርኋቸውስ ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው ምክንያት የላቸውም።
እንግዲህ እኛ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆን በሰው ዕውቀትና ብልሀት በተቀረጸ በድንጋይና በብር፥ በወርቅም አምላክነቱን ልንመስለው አይገባም።
አንተ ሰው ሆይ፥ እውነት ለሚፈርደው ለእግዚአብሔር ምን ትመልስለታለህ? በወንድምህ ላይ የምትጠላውን ያን ሥራ አንተ ራስህ ከሠራኸው በራስህ የምትፈርድ አይደለምን? አንተ ራስህ ያን ሥራ ትሠራዋለህና።
በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ፤ ከሥራቸውም የተነሣ ይታወቃል፤ ሕሊናቸውም ይመሰክርባቸዋል፤ ይፈርድባቸዋልም።
እንግዲህ ጥበበኛ ማን ነው? ጸሓፊስ ማን ነው? ይህን ዓለምስ የሚመረምረው ማን ነው? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ስንፍና አላደረገውምን?
ወደ ሰማይ አትመልከት፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰማይ ሁሉ በታች ላሉት አሕዛብ ሁሉ የሰጣቸውን ፀሐይንና ጨረቃን፥ ከዋክብትንና የሰማይን ሠራዊት ሁሉ አይተህ፥ ሰግደህላቸው፥ አምልከሃቸውም እንዳትስት ተጠንቀቅ።
እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም፤ ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኀይል ይሁን፤ አሜን።
ነውር የሌለው ሆኖ፥ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ይልቅ ያነጻ ይሆን?