ሐዋርያት ሥራ 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ምዕራፍ 22። 1 “እናንተ ወንድሞችና አባቶች፥ አሁን በፊታችሁ የምናገረውን ስሙኝ።” 2 በዕብራይስጥ ቋንቋ እንደሚነግራቸው በሰሙም ጊዜ ጸጥ ብለው አዳመጡት። 3 ጳውሎስም እንዲህ አላቸው፥ “እኔ አይሁዳዊ ሰው ነኝ፤ የቂልቅያ ክፍል በምትሆን በጠርሴስ ከተማ ተወለድሁ፤ በዚችም ከተማ ከገማልያል እግር ሥር ሆኜ አደግሁ፤ የአባቶችንም ሕግ ተማርሁ፤ እናንተ ሁላችሁ ዛሬ እንደምታደርጉትም ለእግዚአብሔር ቀናተኛ ነበርሁ። 4 ይህን ትምህርት የሚከተሉ ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወህኒ ቤት አሳልፌ በመስጠት እስከ ሞት ድረስ አሳደድኋቸው። 5 እንዲቀጡም ከዚያ ያሉትን አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ወደ አሉ ወንድሞች እንድሄድ ከእነርሱ ዘንድ የሥልጣን ደብዳቤ የተቀበልኋቸው ሊቀ ካህናቱና መምህራን ሁሉ ይመሰክራሉ። ስለ መጠራቱ 6 “ከዚህ በኋላ ወደ ደማስቆ ስሄድ ቀትር በሆነ ጊዜ ወደ ከተማው አቅራቢያ ደርሼ ሳለሁ ድንገት ታላቅ መብረቅ ከሰማይ በእኔ ላይ አንፀባረቀ። 7 በምድር ላይም ወደቅሁ ‘ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ቃልንም ሰማሁ። 8 እኔም መልሼ፦ ‘አቤቱ፥ አንተ ማነህ?’ አልሁት፤ እርሱም፦ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ። 9 አብረውኝ የነበሩትም መብረቁን አይተው ደነገጡ፤ ነገር ግን ይናገረኝ የነበረውን ቃል አልሰሙም። 10 ‘አቤቱ፥ ጌታዬ ምን ላድርግ?’ አልሁ፤ ጌታም፦ ‘ተነሥና ወደ ደማስቆ ሂድ፤ ልታደርገው የሚገባህንም ሁሉ በዚያ ይነግሩሃል’ አለኝ። 11 ከዚያም በኋላ ከመብረቁ ነፀብራቅ የተነሣ ዐይኔን ታወርሁ፤ አብረውኝ የነበሩትም እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ። 12 “እንደ ሕጉም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በደማስቆም የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ ያመሰግኑት ነበር። 13 ወደ እኔም መጥቶ በፊቴ ቆመና፦ ‘ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ’ አለ፤ ያንጊዜም ወደ እርሱ አየሁ። 14 እንዲህም አለኝ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅና ጽድቁንም ታይ ዘንድ፥ ቃሉንም ከአንደበቱ ትሰማ ዘንድ መረጠህ። 15 በሕዝብም ሁሉ ዘንድ ባየኸውና በሰማኸው ምስክር ትሆነዋለህ። 16 አሁንም የምታደርገውን ልንገርህ፦ ተነሥ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኀጢአትህም ታጠብ።’ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መመለሱ 17 “ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ በቤተ መቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ። 18 ‘ስለ እኔ የምትመሰክረውን ምስክርነት አይቀበሉህምና ከኢየሩሳሌም ፈጥነህ ውጣ’ ሲለኝ አየሁት። 19 እኔም እንዲህ አልሁት፦ ‘ጌታዬ ሆይ፥ በአንተ የሚያምኑትን በየምኵራቦቻቸው ሳስራቸውና ስደበድባቸው የነበርሁ እኔ እንደ ሆንሁ እነርሱ ያውቃሉ። 20 ሰማዕትህን እስጢፋኖስን በገደሉትም ጊዜ እኔ እዚያ አብሬአቸው ነበርሁ፤ የገዳዮችንም ልብስ እጠብቅ ነበር።’ 21 እርሱም፦ ‘ሂድ ርቀው ወደ አሉ አሕዛብ እልክሃለሁና’ ” አለኝ። 22 ከጳውሎስም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ “ይህ በሕይወት ሊኖር አይገባውምና እንዲህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው” እያሉ ጮሁ። 23 እነርሱም እየጮሁና ልብሳቸውንም እየወረወሩ ትቢያውን ወደ ላይ ሲበትኑ፥ 24 የሻለቃው የሚጮሁበት ስለ ምን እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ ወደ ወታደሮች ሰፈር እንዲያገቡትና እየገረፉ የሠራውን እንዲመረምሩት አዘዘ። 25 ሊገርፉትም በአጋደሙት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የነበረውን የመቶ አለቃ፥ “የሮማን ሰው ያለ ፍርድ ልትገርፉ ይገባችኋልን?” አለው። 26 የመቶ አለቃውም ይህን በሰማ ጊዜ፥ ወደ ሻለቃው ሄደና፥ “ይህ ሰው ሮማዊ ነው፥ የምታደርገውን ዕወቅ” ብሎ ነገረው። 27 የሻለቃውም ወደ እርሱ ቀርቦ፥ “አንተ ሮማዊ ነህን? እስኪ ንገረኝ” አለው፤ ጳውሎስም፥ “አዎን” አለው። 28 የሻለቃውም መልሶ፥ “እኔ ይህችን ዜግነት ያገኘኋት ብዙ ገንዘብ ሰጥቼ ነው” አለው፤ ጳውሎስም፥ “እኔማ የተወለድሁ በዚያው ነው” አለው። 29 ከዚህም በኋላ ይመረምሩት ዘንድ የሚሹት ተዉት፤ የሻለቃውም ሮማዊ መሆኑን በዐወቀ ጊዜ“ ለምን አሰርሁት?” ብሎ ፈራ። 30 በማግሥቱም የሻለቃው አይሁድ የሚከሱት ስለ ምን እንደሆነ ያውቅ ዘንድ ወደደና ከእስራቱ ፈታው፤ ሊቃነ ካህናቱና ሸንጎውም ሁሉ እንዲመጡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም አምጥቶ በፊታቸው አቆመው። |