ራእይ 7:12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “አሜን በረከትና ገናናነት ጥበብም ምስጋናም ክብርም ኀይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን! አሜን።” አሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንዲህም ይሉ ነበር፤ “አሜን፤ ውዳሴና ክብር፣ ጥበብ፣ ምስጋናና፣ ሞገስ፣ ኀይልና ብርታትም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን። አሜን።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “አሜን ውዳሴ፥ ክብር፥ ጥበብ፥ ምስጋና ገናናነት፥ ክብር ኃይልና ብርታት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን! አሜን።” አሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንዲህም አሉ፦ “አሜን! ውዳሴ፥ ገናናነት፥ ጥበብ፥ ምስጋና፥ ክብር፥ ኀይል፥ ብርታት ለአምላካችን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ። |
ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ደስ አሰኝሻለሁ፤ ባድማሽንም ሁሉ ደስ አሰኛለሁ፤ ምድረ በዳሽንም እንደ ዔድን፥ በረሃዎችሽንም እንደ እግዚአብሔር ገነት አደርጋለሁ። ደስታና ተድላ እምነትና የዝማሬ ድምፅ በውስጧ ይገኝባታል።
የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ፦ እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ሰዎች ድምፅ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡ ሰዎች ድምፅ እንደ ገና ይሰማል። የዚያችን ምድር ምርኮኞች ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር።
ይህችም ከተማ እኔ የምሠራላቸውን በጎነት ሁሉ በሚሰሙ፥ እኔም ስላመጣሁላቸው በጎነትና ሰላም ሁሉ በሚፈሩና በሚደነግጡ አሕዛብ ሁሉ ፊት ለደስታ፥ ለክብርና ለገናንነት ትሆናለች።”
አንተ በመንፈስ ብታመሰግን፥ ያ የቆመው ያልተማረው በአንተ ምስጋና ላይ እንዴት አሜን ይላል? የምትናገረውንና የምትጸልየውን አያውቅምና።
በቃልም ቢሆን፥ ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድርጉ፤ ስለ እርሱም እግዚአብሔር አብን አመስግኑት።
ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኀይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።