ዮናስ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጸሎተ ዮናስ 1 እግዚአብሔርም ዮናስን ይውጠው ዘንድ ታላቅ ዓሣ አንበሪን አዘዘ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ነበረ። 2 ዮናስም በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እንዲህም አለ፦ 3 “በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ የጩኸቴን ድምፅ ሰማኝ፤ ቃሌንም አዳመጥህ። 4 ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ፥ ፈሳሾችም ከበቡኝ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ ዐለፉ። 5 እኔም፦ ከዐይንህ ፊት ተጣልሁ፤ ነገር ግን ወደ ቅዱስ መቅደስህ ደግሞ እመለከታለሁን? አልሁ። 6 ውኃ እስከ ነፍሴ ድረስ ፈሰሰ፤ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ከበበኝ፤ 7 እነሆ ራሴ ወደ ታች ወደ ተራሮች መሠረት ወረደ፤ ከጥንት ጀምሮ መወርወሪያዎችዋ ወደ ተዘጉ ምድር ወረድሁ፤ አቤቱ ፈጣሪዬ! ሕይወቴ ጥፋት ሳያገኛት ወዳንተ ትውጣ። 8 ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን አሰብሁት፤ ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ትግባ። 9 ከንቱነትንና ሐሰትን የሚጠብቁ፤ ይቅርታቸውን ትተዋል። 10 እኔ ግን ከምስጋናና ከኑዛዜ ቃል ጋር እሠዋልሃለሁ፤ የድኅነቴ አምላክ ሆይ! የተሳልሁትን ለአንተ እከፍላለሁ።” 11 እግዚአብሔርም ዓሣ አንበሪውን አዘዘው፤ እርሱም ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው። |