ማቴዎስ 26:39 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ “አባቴ! ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን፤” አለ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ወደ ፊት ጥቂት እልፍ ብሎ በፊቱ ተደፋና እንዲህ ሲል ጸለየ “አባቴ! የሚቻል ከሆነ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ አይሁን።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደና፥ በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፥ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ጽዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። |
ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትና ሽማግሌዎቹም ማቅ ለብሰው በግንባራቸው ተደፉ።
ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፤ ከኀያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ኀጢአታቸውም ተሰጠ።
በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ አለ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። በአየሁም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ። የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።
እነርሱም በግንባራቸው ወድቀው፥ “የነፍስና የሥጋ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንድ ሰው ኀጢአት ቢሠራ የእግዚአብሔር ቍጣ በማኅበሩ ላይ ይሆናልን?” አሉ።
ኢየሱስ ግን መልሶ “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አለ። “እንችላለን” አሉት።
ድንጋዩንም አነሡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አቅንቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ፥ ሰምተኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል።
እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ እንጂ፤ ፍርዴም እውነት ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና።
እርሱም ሥጋ ለብሶ በዚህ ዓለም በነበረበት ጊዜ፥ በታላቅ ጩኸትና እንባ ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ ጽድቁንም ሰማው።
ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና፤” አለኝ።