ዮሐንስ 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ስለ መስጠቱ 1 ጌታችን ኢየሱስም ይህን ተናግሮ አትክልት ወደ አለበት ስፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደዚያ ገባ። 2 አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ያን ስፍራ ያውቀው ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደዚያ ብዙ ጊዜ ይሄድ ነበርና። 3 ይሁዳም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ወታደሮችን ተቀበለ፤ ሎሌዎቻቸውንም በረዳትነት ወሰደ፤ ፋኖስና የችቦ መብራት፥ የጦር መሣሪያም ይዞ ወደዚያ ሄደ። 4 ጌታችን ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጣና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” አላቸው። 5 “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” አላቸው፤ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም በዚያው አብሮአቸው ቆሞ ነበር። 6 ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ፤ ወደ ኋላቸው ተመልሰው በምድር ላይ ወደቁ። 7 ከዚህም በኋላ እንደገና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም፥ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። 8 ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እኔን የምትሹ ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አላቸው። 9 ይህም፥ “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንድ ስንኳ አልጠፋም” ያለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ ነው። 10 ስምዖን ጴጥሮስም ሾተል ነበረው፤ ሾተሉንም መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው፤ የዚህም አገልጋይ ስም ማልኮስ ይባል ነበር። 11 ጌታችን ኢየሱስም ጴጥሮስን፥ “ሾተልህን ወደ አፎቷ መልስ፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ ሳልጠጣ እተወዋለሁን?” አለው። ወደ ሊቃነ ካህናት ስለ መሄዱ 12 ጭፍሮችና የሺ አለቃው፥ የአይሁድም ሎሌዎች ጌታችን ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። 13 አስቀድሞም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። 14 ቀያፋም “ስለ ሕዝቡ ሁሉ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል” ብሎ አይሁድን የመከራቸው ነበር። ስለ ጴጥሮስ ክህደት 15 ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙርም ጌታችን ኢየሱስን ከሩቅ ተከተሉት፤ ያ ደቀ መዝሙር ግን በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ከጌታችን ኢየሱስ ጋርም ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ። 16 ጴጥሮስ ግን በስተውጭ በበሩ ቆሞ ነበር፤ ያም በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ይታወቅ የነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣና ለበረኛዪቱ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። 17 በረኛዪቱ አገልጋይም፥ “አንተም ከዚያ ሰው ደቀ መዛሙርት ወገን አይደለህምን?” አለችው፤ እርሱም፥ “አይደለሁም” አላት። 18 አገልጋዮችና ሎሌዎችም በዚያ ቆመው እሳት አንድደው ይሞቁ ነበር፤ የዚያች ሌሊት ብርድ ጽኑ ነበርና፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበረ። ሊቀ ካህናቱ እንደ ጠየቀው 19 ሊቀ ካህናቱም ጌታችን ኢየሱስን፦ ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። 20 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እኔ ለዓለም በግልጥ ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብም፥ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም የተናገርሁት አንዳች ነገር የለም። 21 እንግዲህ እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? የተናገርሁትን የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እኔም የተናገርሁትን እነሆ፥ እነርሱ ያውቃሉ።” 22 ይህንም ባለጊዜ ከቆሙት ሎሌዎች አንዱ፥ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልስለታለህን?” ብሎ ጌታችን ኢየሱስን በጥፊ መታው። 23 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። 24 ሐናም ጌታችን ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። 25 ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፤ “አንተስ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት ወገን አይደለህምን?” አሉት፤ እርሱም፥ “አይደለሁም” ብሎ ካደ። 26 ጴጥሮስ ጆሮውን ከቈረጠው ሰው ዘመዶች ወገን የሆነ ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮችም አንድ ሰው፥ “እኔ በአትክልት ቦታ ውስጥ ከእርሱ ጋር አይችህ አልነበረምን?” አለው። 27 ጴጥሮስም ደግሞ ካደ፤ ያንጊዜም ዶሮ ጮኸ። ጌታ በጲላጦስ ፊት ስለ መቆሙ 28 ጌታችን ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ፍርድ አደባባይ ወሰዱት፤ አይሁድ ግን ፈጽሞ ስለ ነጋ የፋሲካውን በግ ሳይበሉ እንዳይረክሱ ወደ ፍርድ አደባባይ አልገቡም። 29 ጲላጦስም ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጥቶ፥ “ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደሉ ምንድነው?” አላቸው። 30 እነርሱም፥ “ክፉ የሠራ ባይሆንስ ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነው ነበር” ብለው መለሱለት። 31 ጲላጦስም፥ “እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው፤ አይሁድም፥ “እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም” አሉት። 32 ይህም በምን ዐይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው የጌታችን የኢየሱስ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 33 ጲላጦስም እንደገና ወደ ፍርድ አደባባይ ገብቶ ጌታችን ኢየሱስን ጠራና፥ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። 34 ጌታችን ኢየሱስም፥ “ይህን የምትናገር ከራስህ ነውን? ወይስ ስለ እኔ የነገረህ ሌላ አለን?” ብሎ መለሰለት። 35 ጲላጦስም መልሶ፥ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ ወገኖችህና ሊቃነ ካህናት አይደሉምን? Aረ ምን አድርገሃል?” አለው። 36 ጌታችን ኢየሱስም፥ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ በዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ ለአይሁድ እንዳልሰጥ አሽከሮች በተዋጉልኝ ነበር፤ አሁንም መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” ብሎ መለሰለት። 37 ጲላጦስም፥ “እንግዲያ አንተ ንጉሥ ነህን?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ራስህ ትላለህ፤ እኔ ስለዚህ ተወለድሁ፤ ስለዚህም ለእውነት ልመሰክር ወደ ዓለም መጣሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማኛል” አለው። 38 ጲላጦስም፥ “እውነት ምንድነው?” አለው፤ ይህንም ተናግሮ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጣና እንዲህ አላቸው፥ “እኔ አንዲት ስንኳን በደል አላገኘሁበትም። 39 ነገር ግን በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ከእስረኞች አንድ እንድፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?” አላቸው። 40 ዳግመኛም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፥ “በርባንን እንጂ ይህን አይደለም፤” አሉ፤ በርባን ግን ወንበዴ ነበር። |