ኤርምያስ 33:6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነሆ ፈውስንና መድኀኒትን እሰጣታለሁ፤ እፈውሳታለሁም፤ የሰላምንና የእውነትንም መንገድ እገልጥላቸዋለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ ‘ይሁን እንጂ፣ ፈውስንና ጤንነትን እንደ ገና እሰጣታለሁ፤ ሕዝቤንም እፈውሳለሁ፤ በብዙ ሰላምና በርጋታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነሆ፥ ፈውስንና መድኃኒትን አመጣላታለሁ፥ እፈውሳቸዋለሁም፤ እጅግም የበዛ ሰላምንና እውነትን እገልጥላቸዋለሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነገር ግን ይህችን ከተማና ሕዝብዋን እንደገና እፈውሳለሁ፤ ጤንነታቸውንም እመልስላቸዋለሁ፤ በሁሉም ቦታ ሰላምንና የሕይወት ዋስትናን አበዛላቸዋለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነሆ፥ ፈውስንና መድኃኒትን አመጣላታለሁ፥ እፈውሳቸውማለሁ፥ የሰላምንና የእውነትን ብዛት እገልጥላቸዋለሁ። |
በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፤ ብዙ አሕዛብንም ይዘልፋቸዋል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍን አያነሣም፤ ሰልፍንም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።
እግዚአብሔርም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ በመቅሠፍቱ የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይሆናል።
ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ “እርሱ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው፤ ነገር ግን፦ በዘመኔ ሰላምና ጽድቅ ይሁን” አለው።
ክፉ ሰው መንገዱን፥ በደለኛም ዐሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ፤ እርሱም ይምረዋል፤ እርሱ ብዙ በደላችሁን ይተውላችኋልና።
ያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፤ ፈውስህም ፈጥኖ ይወጣል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይጋርድሃል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “እነሆ፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ልጆቻቸውንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል፤ በጕልበታቸውም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሏቸዋል።
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።
“ከዳተኞች ልጆች ሆይ! ተመለሱ፤ ቍስላችሁንም እፈውሳለሁ። እነሆ እኛ አገልጋዮችህ እንሆናለን፤ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና።
በመከራቸው ጊዜ በማለዳ ወደ እኔ ይገሰግሳሉ፤ እንዲህም ይላሉ፥ “ኑ፤ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናልና፥ እርሱም ይጠግነናል።
በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኀጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ።
በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፥ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፥ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም።
ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፣ እናንተም ትወጣላችሁ፥ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ።
ሌባ ግን ሊሰርቅና ሊያርድ፥ ሊያጠፋም ካልሆነ በቀር አይመጣም፤ እኔ ግን የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኙ፥ እጅግም እንዲበዛላቸው መጣሁ።
ከአባታችን ከእግዚአብሔር አብ፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ከእምነት ጋር ሰላምና ፍቅር ለወንድሞቻችን ይሁን።
እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ ዕወቁ፤ ዕወቁ። እኔ እገድላለሁ፤ አድንማለሁ፤ እኔ እገርፋለሁ፤ ይቅርም እላለሁ፤ ከእጄም የሚያመልጥ የለም።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኀይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።