ኢሳይያስ 39 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች 1 በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ ታምሞ እንደ ተፈወሰ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻን፥ መልእክተኞችንም ላከለት። 2 ሕዝቅያስም ስለ እነርሱ እጅግ ደስ አለው፤ ግምጃ ቤቱንም፥ ወርቁንና ብሩን፥ ከርቤውንና ዕጣኑን፥ ዘይቱንም፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት ሁሉ፥ ልብሱንና ዕንቍውን ሁሉ፥ በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው፤ በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም። 3 ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ፥ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡ?” አለው። ሕዝቅያስም፥ “ከሩቅ ሀገር ከባቢሎን መጡ” አለው። 4 ኢሳይያስም፥ “በቤትህ ያዩት ምንድን ነው?” አለው፤ ሕዝቅያስም፥ “በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤቴ፥ እንዲሁም በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም” አለው። 5 ኢሳይያስም ሕዝቅያስን፥ “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። 6 እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አያስቀሩልህም፤ ይላል እግዚአብሔር። 7 ከአንተ ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦችና የቤት አሽከሮች ይሆናሉ” አለው። 8 ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ “እርሱ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው፤ ነገር ግን፦ በዘመኔ ሰላምና ጽድቅ ይሁን” አለው። |