መዝሙር 67 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ይነሣ፥ ጠላቶቹም ይበተኑ፥ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ። 2 ጢስ እንደሚበንን እንዲሁ ይብነኑ፤ ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ ኃጥኣን ከአግዚአብሔር ፊት ይጥፉ። 3 ጻድቃን ግን ደስ ይበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤትን ያድርጉ፥ በደስታም ደስ ይበላቸው። 4 እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለስሙም ዘምሩ፤ ወደ ምዕራብ ለወጣው መንገድን አብጁ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው፥ በፊቱም ደስ ይበላችሁ፤ ከፊቱም የተነሣ ይደነግጣሉ። 5 እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሃ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው። 6 እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤቱ ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኀይሉ ያወጣቸዋል፤ በመቃብር የሚኖሩ ኀዘንተኞችንም እንዲሁ። 7 አቤቱ፥ በሕዝብህ ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ 8 ከሲና አምላክ ፊት፥ ከእስራኤል አምላክ ፊት ምድር ተናወጠች፥ ሰማያትም አንጠባጠቡ። 9 አቤቱ፥ በፈቃድህ ዝናብን ለርስትህ ለየህ፥ በደከመም ጊዜ አንተ ታጸናዋለህ። 10 እንስሶችህ በውስጡ ያድራሉ፤ አቤቱ፥ በቸርነትህ ለድሆች አዘጋጀህ። 11 ብዙ ኀይልን ለሚያወሩ እግዚአብሔር ቃሉን ሰጠ፤ 12 ለኀያላን ንጉሥ ለወዳጁ፤ ለወዳጁና ለቤትህ ውበት ምርኮን ተካፈልን። 13 በርስቶች መካከል ብታድሩ፥ ከብር እንደ ተሠሩ እንደ ርግብ ክንፎች፥ በቅጠልያ ወርቅም እንደ ተለበጡ ላባዎችዋ ትሆናላችሁ። 14 ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ፥ በሰልሞን ላይ በረዶ ይዘንማል። 15 የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፤ የጸና ተራራና የለመለመ ተራራ ነው። 16 የጸኑ ተራራዎች ለምን ይነሣሉ? እግዚአብሔር ያድርበት ዘንድ የወደደው ተራራ ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ያድርባቸዋልና። 17 የብዙ ብዙ ሺህ የእግዚአብሔር ሰረገላዎች ደስተኞች ናቸው። እግዚአብሔር በመቅደሱ በሲና በመካከላቸው ነው። 18 ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ወጣህ ስጦታህንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ያድሩ ዘንድ ይክዱ ነበርና። 19 እግዚአብሔር አምላክ ቡሩክ ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው፤ አምላካችንና መድኃኒታችን ይረዳናል። 20 አምላካችንስ የማዳን አምላክ ነው፤ የሞት መንገድ የእግዚአብሔር ነው። 21 ነገር ግን እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ ይሰብራል፥ በጠጉራቸው ጫፍም በደላቸው ይሄዳል። 22 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ ወጥቼ እመለሳለሁ፥ በባሕሩም ጥልቅ እመለሳለሁ፥ 23 እግሮችህ በደም ይነከሩ ዘንድ፥ የውሾችህ ምላስ በጠላቶችህ ላይ ነው። 24 አቤቱ፥ መንገድህ ተገለጠ። የአምላካችን የንጉሡ መንገድ በመቅደሱ 25 አለቆች ደረሱ፥ መዘምራንም አሏቸው ከበሮን በሚመቱ በደናግል መካከል። 26 እግዚአብሔርን በጉባኤ፥ አምላካችንንም በእስራኤል ምንጮች አመሰገኑት። 27 ወጣቱ ብንያም በጉልበቱ በዚያ አለ፥ ገዦቻቸው የይሁዳ አለቆች፥ የዛብሎን አለቆችና የንፍታሌምም አለቆች። 28 አቤቱ፥ በኀይልህ እዘዝ፤ አቤቱ፥ ይህን ለእኛ የሠራኸውን አጽናው። 29 በኢየሩሳሌም ባለው መቅደስህ ነገሥታት እጅ መንሻን ለአንተ ያመጣሉ። 30 በቀርካሃ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በሕዝብ ጊደሮች መካከል የበሬዎችን ጉባኤ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፤ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው። 31 መልእክተኞች ከግብፅ ይምጡ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። 32 የምድር ነገሥታት እግዚአብሔርን አመስግኑት፥ ለአምላካችንም ዘምሩ። 33 በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኀይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል። 34 ለእግዚአብሔር ምስጋናን ስጡ፤ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኀይሉም እስከ ደመናት ነው። 35 እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እርሱ ኀይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ይመስገን። |