ኤርምያስ 31:23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ ሀገር በከተሞችዋ፦ የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክህ የሚል ነገርን እንደ ገና ይናገራሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምርኳቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣ እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ፦ ‘የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! ጌታ ይባርክህ’ የሚልን ቃል እንደገና ይናገራሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡን ወደ አገራቸው በመለስኩ ጊዜ በይሁዳና በከተሞቹ እንደገና ‘አንቺ የእውነት ማደሪያ የሆንሽ ቅድስት ተራራ እግዚአብሔር ይባርክሽ’ ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ፦ የጽድቅ ማደሪያ ሆይ፥ የቅድስና ተራራ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ የሚልን ነገር እንደ ገና ይናገራሉ። |
ፍርድ መልቶባት የነበረ የታመነችይቱ የጽዮን ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፤ አሁን ግን ወንበዴዎችና ነፍሰ ገዳዮች አሉባት።
ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ፥ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያ ጊዜ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ፥ የታመነችም ጽዮን ርእሰ ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።
እነርሱም አይጐዱትም፤ በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ማንንም አይጐዱም፤ አያጠፉምም፤ ብዙ ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።
እገለጥላችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፤ ከአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እናንተንም ከበተንሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማዪቱም በጕብታዋ ላይ ትሠራለች፤ አዳራሹም እንደ ዱሮው የሰው መኖሪያ ይሆናል።
ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና በብንያም ሀገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በደጋውም ባሉ ከተሞች፥ በቆላውም ባሉ ከተሞች፥ በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ፤ በውሉም ወረቀት ፈርመው ያትማሉ፤ ምስክሮችንም ያቆማሉ፤” ይላል እግዚአብሔር።
ያገኙአቸው ሁሉ በሉአቸው፤ ጠላቶቻቸውም፦ በጽድቅ ማደሪያ በእግዚአብሔር ላይ፥ በአባቶቻቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ስለ ሠሩ እኛ አናሳርፋቸውም አሉ።
“ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ መድኀኒት ይሆናል፤ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፤ የያዕቆብም ቤት ሰዎች የወረሱአቸውን ይወርሳሉ።
በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፣ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፣ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል።
እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፥ አጫጆችንም፦ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን አላቸው። እነርሱም፦ እግዚአብሔር ይባርክህ ብለው መለሱለት።