ኢሳይያስ 55:12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ፤ በሐሤትም ትማራላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በደስታ ሊቀበሏችሁ ይዘላሉ፤ የሜዳም ዛፎች ሁሉ በቅርንጫፎቻቸው ያጨበጭባሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በደስታ ትወጣላችሁ፤ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኰረብቶች፣ በፊታችሁ በእልልታ ይዘምራሉ፤ የሜዳ ዛፎች ሁሉ፣ ያጨበጭባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልል ይላሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “እናንተም ከባቢሎን በደስታ ወጥታችሁ፥ በሰላም ወደ ሀገራችሁ እንድትመለሱ ትደረጋላችሁ፤ ተራራዎችና ኰረብቶች በፊታችሁ በመዘመር ይፈነድቃሉ፤ የሜዳ ዛፎችም በእጆቻቸው ያጨበጭባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፥ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። |
በእግዚአብሔር የተሰበሰቡም ይመለሳሉ፤ በደስታም ተመልሰው ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘለዓለም ደስታም በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታንም ያገኛሉ፤ መከራ፥ ኀዘንና ትካዜም ይጠፋሉ።
እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ምሕረትን አድርጎአልና ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና የምድር መሠረቶች መለከትን ይንፉ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በውስጣቸው ያሉ ዛፎች ሁሉ፥ እልል ይበሉ።
ከባቢሎን ውጡ፤ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ፤ ይህም ይሰማ፤ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩና፥ “እግዚአብሔር ባርያውን ያዕቆብን ታድጎታል” በሉ።
እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቅር ብሎአልና፥ ከሕዝቡም ችግረኞቹን አጽንቶአልና። ሰማያት ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ምድርም ደስ ይበላት፤ ተራሮችም እልል ይበሉ።
እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ ወደ ጽዮንም በደስታና በሐሤት ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ክብር በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፤ ኀዘንና ልቅሶም ይወገዳሉ።
ተራሮችን እንዳልቀሥፋቸው እንዳላፈልሳቸውም፥ ኮረብቶችም እንዳይነዋወጡ እንደ ማልሁ እንዲሁ ከእኔ ዘንድ ያለሽ ይቅርታ አያልቅም፤ የሰላምሽ ቃል ኪዳንም አይጠፋም፤ መሓሪሽ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።
የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ፦ እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ሰዎች ድምፅ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡ ሰዎች ድምፅ እንደ ገና ይሰማል። የዚያችን ምድር ምርኮኞች ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር።
እነሆ ፈውስንና መድኀኒትን እሰጣታለሁ፤ እፈውሳታለሁም፤ የሰላምንና የእውነትንም መንገድ እገልጥላቸዋለሁ።
የዱር ዛፎች ሁሉ፥ ረዥሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናገርሁ፤ እኔም አደረግሁ።”
እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኀጢኣተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት ደስታ ይሆናል።”
የተስፋ አምላክ እግዚአብሔርም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በተስፋ ያበዛችሁ ዘንድ በእምነት ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይፈጽምላችሁ።
በዚህ ብቻ አይደለም፤ በእርሱ ይቅርታውን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም በእግዚአብሔር ዘንድ እንመካለን እንጂ።