ኢሳይያስ 12:5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ስም ዘምሩ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ታላቅ ሥራ ሠርቷልና፤ ይህም ለዓለም ሁሉ ይታወቅ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ለጌታ ዘምሩ፤ ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና፤ ይህም ለዓለም ሁሉ ይታወቅ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለ ታላቅ ሥራውም ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ይህም ታላቅ ሥራው በዓለም ሁሉ እንዲታወቅ አድርጉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ታላቅ ሥራ ሰርቶአልና ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ። |
በዚያ ጊዜም ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለእግዚአብሔር እንዘምራለን፤ በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።
ማርያምም አስቀድማ ለእግዚአብሔር እንዘምር አለች፥ “ለእግዚአብሔር እንዘምር በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጥሎአልና።”
እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፤ በምድር የቀሩትም ስለ እግዚአብሔር ክብር በአንድነት ደስ ይላቸዋል፤ የባሕርም ውኃ ይናወጣል።
ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤ ለኢየሩሳሌም የምሥራችን የምትነግር ሆይ፥ ድምፅህን በኀይል አንሣ፤ አትፍራ፤ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለህ ንገር።
ወደ ባሕር የምትወርዱ፥ በእርስዋም ውስጥ የምትጓዙ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤ ከምድርም ዳርቻ ስሙን አክብሩ።
ምድረ በዳውና ከተሞችዋ፥ የቄዳርም ነዋሪዎችና መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በዋሻም የሚኖሩ እልል ይበሉ፤ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ።
እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ምሕረትን አድርጎአልና ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና የምድር መሠረቶች መለከትን ይንፉ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በውስጣቸው ያሉ ዛፎች ሁሉ፥ እልል ይበሉ።
ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፣ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፣ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ! መንገድህ ትክክልና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ! የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፤ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ፤” እያሉ የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ።