ዕብራውያን 11:3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠረ፥ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደ ሆነ በእምነት እናውቃለን። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ዓለማት በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠሩ በእምነት እንረዳለን፤ ስለዚህ የሚታየው ነገር የተፈጠረው ከሚታየው እንዳልሆነ እንገነዘባለን። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠሩ፥ የሚታየውም ነገር ከሚታዩት እንዳልተፈጠረ በእምነት እንረዳለን። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠረ የምንረዳው በእምነት ነው። ስለዚህ የሚታየው ነገር ሁሉ ከማይታየው እንደ ተሠራ እናውቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። |
ዐይናችሁን ወደ ሰማይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ ይህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? ከዋክብትንም በሙሉ የሚቈጥራቸው እርሱ ነው፤ በየጊዜያቸው ያመጣቸዋል፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በክብሩ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።
እናንተም፦ ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ፥ ከሰማይም በታች ፈጽመው ይጥፉ ትሉአቸዋላችሁ።
የያዕቆብ ዕድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ ሁሉን የፈጠረ ነውና እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
እንዲህም አሉአቸው፥ “እናንተ ሰዎች፥ ይህን ነገር ለምን ታደርጋላችሁ? እኛስ እንደ እናንተ የምንሞት ሰዎች አይደለንምን? ነገር ግን ይህን ከንቱ ነገር ትታችሁ ሰማይና ምድርን፥ ባሕርንም በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ ወንጌልን እናስተምራችኋለን።
“ለብዙዎች አሕዛብ አባት አደርግሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ሙታንን በሚያስነሣቸው፥ የሌሉትንም እንደ አሉ በሚያደርጋቸው በአመነበት በእግዚአብሔር ፊት አብርሃም የሁላችን አባት ነው።
ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔር ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።