ቈላስይስ 1:9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ስለዚህም እኛ ዜናችሁን ከሰማን ጀምሮ፥ በፍጹም ጥበብና በፍጹም መንፈሳዊ ምክር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅን ትፈጽሙ ዘንድ፥ ስለ እናንተ መጸለይንና መለመንን አልተውንም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ስለዚህ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የፈቃዱን እውቀት እንድትሞሉ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እናንተ በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምትገነዘቡበት ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራችሁ ለእናንተ ከመጸለይና እግዚአብሔርን ከመለመን አላቋረጥንም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ |
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድድ ግን ትምህርቴ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ሆነች፥ የምናገረውም ከራሴ እንዳይደለ እርሱ ያውቃል።
ይህን ዓለም አትምሰሉ፤ ልባችሁንም አድሱ፤ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን፥ ፍጹሙንም መርምሩ።
የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሮች እንጂ ለሰው ደስ እንደሚያሰኝ ለታይታ አይደለም።
ይህም ወደ እናንተ የደረሰውን የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ከአያችሁበት ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያድግና ያፈራ ዘንድ ነው።
በጥበብ ሁሉ እንድትበለጽጉ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ዘንድ ይጽና፤ በመንፈስም ራሳችሁን አስተምሩ፤ ገሥፁ፤ መዝሙርንና ምስጋናን፥ የቅድስና ማሕሌትንም በልባችሁ በጸጋ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
ከእናንተ ወገን የሚሆን ኤጳፍራስም ሰላም ይላችኋል፥ እርሱ የክርስቶስ አገልጋይ ነው፤ እግዚአብሔር በሚወደው ነገር ሁሉ ምሉኣንና ፍጹማን እንድትሆኑ፥ ስለ እናንተ ዘወትር ይጸልያል፤ ይማልዳልም።
ስለዚህም ደግሞ እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥ አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ የእምነትንም ሥራ በኀይል ይፈጽም ዘንድ ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን።
በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ፥ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤
የሰላም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።
የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አሳያችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይንና እግዚአብሔርን ማገልገልን በመተው እርሱን እበድል ዘንድ እግዚአብሔር ይህን አያድርግብኝ።