1 ተሰሎንቄ 4:3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት ርቃችሁ እንድትቀደሱ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፥ እርሱም መቀደሳችሁ፥ ከዝሙትም መራቃችሁ ነው፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የእግዚአብሔር ፈቃድ እናንተ እንድትቀደሱና ከዝሙት እንድትርቁ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ |
ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፥ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድድ ግን ትምህርቴ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ሆነች፥ የምናገረውም ከራሴ እንዳይደለ እርሱ ያውቃል።
ነገር ግን ለጣዖት ከሚሠዋው፥ ከዝሙት፥ ሞቶ የተገኘውንና ደም ከመብላት እንዲርቁ፥ ለራሳቸው የሚጠሉትንም በወንድሞቻቸው ላይ እንዳያደርጉ እዘዙአቸው።
ለአማልክት የተሠዋውን፥ ሞቶ የተገኘውን፥ ደምንም አትብሉ፤ ከዝሙትም ራቁ፤ በራሳችሁ የምትጠሉትንም በወንድሞቻችሁ ላይ አታድርጉ፥ ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ በሰላም ትኖራላችሁ፤ ደኅና ሁኑ።”
አሁንም ለእግዚአብሔርና ሊያንጻችሁ፥ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ሊሰጣችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።
ይኸውም ዐይናቸውን ትከፍትላቸው ዘንድ፥ ከጨለማም ወደ ብርሃን፥ ሰይጣንን ከማምለክም ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸው ዘንድ፥ ኀጢአታቸውም ይሰረይላቸው ዘንድ፥ በስሜም በማመን ከቅዱሳን ጋር አንድነትን ያገኙ ዘንድ ነው።’
እነርሱም ዐመፅን ሁሉ፥ ክፋትንም፥ ምኞትንም፥ ቅሚያንም፥ ቅናትንም የተመሉ ናቸው፤ ምቀኞች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ከዳተኞች፥ ተንኰለኞች፥ ኩሩዎች፥ ጠባያቸውንና ግብራቸውንም ያከፉ ናቸው።
ይህን ዓለም አትምሰሉ፤ ልባችሁንም አድሱ፤ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን፥ ፍጹሙንም መርምሩ።
ዛሬ ግን ከኀጢአት ነጻ ወጣችሁ፤ ራሳችሁንም ለጽድቅ አስገዛችሁ፤ ለቅድስናም ፍሬን አፈራችሁ፤ ፍጻሜው ግን የዘለዓለም ሕይወት ነው።
እናንተም በኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ናችሁ፤ በእርሱም ከእግዚአብሔር ጥበብንና ጽድቅን፥ ቅድስናንና ቤዛነትን አገኘን።
ወይም እንደ ገና ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር ያሳዝነኝ ይሆናል፤ በድለው ንስሓ ላልገቡም ስለ ርኵስነታቸውና ስለ መዳራታቸው፥ ስለሚሠሩት ዝሙታቸውም ለብዙዎች አዝን ይሆናል።
የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሮች እንጂ ለሰው ደስ እንደሚያሰኝ ለታይታ አይደለም።
ስለዚህም እኛ ዜናችሁን ከሰማን ጀምሮ፥ በፍጹም ጥበብና በፍጹም መንፈሳዊ ምክር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅን ትፈጽሙ ዘንድ፥ ስለ እናንተ መጸለይንና መለመንን አልተውንም።
ከእናንተ ወገን የሚሆን ኤጳፍራስም ሰላም ይላችኋል፥ እርሱ የክርስቶስ አገልጋይ ነው፤ እግዚአብሔር በሚወደው ነገር ሁሉ ምሉኣንና ፍጹማን እንድትሆኑ፥ ስለ እናንተ ዘወትር ይጸልያል፤ ይማልዳልም።
ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤
የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።
እኛ ግን በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ! ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፤ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤
መድኃኒታችንም ከዐመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።
የሰላም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፥ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለውም፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።
ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።”