1 ሳሙኤል 6:3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነርሱም፥ “የእስራኤልን አምላክ የቃል ኪዳኑን ታቦት ብትሰድዱአት ስለ አሳዘናችሁአት የበደል መባእ ስጡ እንጂ ባዶዋን አትስደዱአት፤ የዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፤ ስርየትም ይደረግላችኋል፤ አለዚያ ግን የእግዚአብሔር እጅ ከእናንተ አይርቅም” አሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነርሱም፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ከበደል መሥዋዕት ጋራ ስደዱት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፤ በዚያ ጊዜ ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ ላይ ለምን እንዳልተነሣ ታውቃላችሁ” አሏቸው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነርሱም፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ከበደል መሥዋዕት ጋር ስደዱት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፤ በዚያን ጊዜ ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ ላይ ለምን እንዳልተነሣ ታውቃላችሁ” አሏቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “የእስራኤልን አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት መልሳችሁ ለመላክ ብትፈልጉ፥ ስለ በደላችሁ የሚከፈል ስጦታ አብራችሁ መላክ ይገባችኋል፤ የቃል ኪዳኑ ታቦት ያለ ምንም ስጦታ ተመልሶ መሄድ የለበትም፤ በዚህም ዐይነት እናንተ ከሕመማችሁ ትፈወሳላችሁ፤ እርሱ እናንተን በብርቱ የቀጣበትንም ምክንያት ልታውቁ ትችላላችሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነርሱም፦ የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰድዱ የበደል መሥዋዕት መልሱለት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፥ የዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፥ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ አሉ። |
የቂጣውን በዓል ጠብቁ፤ በአዲስ ወር ከግብፅ ምድር ወጥታችኋልና በዚህ ወር እንዳዘዝኋችሁ ሰባት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ።
የአህያውንም በኵር በበግ ትዋጀዋለህ፤ ባትዋጀው ግን ዋጋውን ትሰጣለህ። የልጆችህንም በኵር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴም ባዶ እጅህን አትታይ።
እግዚአብሔርን ስለ መበደሉና ስለ ሠራው ኀጢአት ከበጎቹ ነውር የሌለባትን እንስት በግ ወይም ከፍየሎች እንስት ፍየል ያመጣል፤ ካህኑም ስለ ኀጢአቱ ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል።
ስለ በደል መሥዋዕትም ከመንጋው ነውር የሌለበትን፥ ዋጋው እንደ በደሉ የተገመተውን አውራ በግ ለእግዚአብሔር ያምጣ።።
በዓመት ሦስት ጊዜ በቂጣ በዓል፥ በሰባቱ ሱባዔም በዓል፥ በዳስም በዓል ወንድ ልጅህ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ይታይ፤
ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱአት፤ እኛንና ሕዝባችንን እንዳትገድል በስፍራዋ ትቀመጥ” አሉ።
የአዛጦንም ሰዎች እንዲህ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ፥ “እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አትቀመጥ” አሉ።
ከሄደችም በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በከተማዪቱ ላይ መጣች፤ ታላቅ ሁከትም ሆነ፤ የከተማዪቱንም ሰዎች ታላቁንም ታናሹንም መታ፤ የውስጥ አካላቸውንም በእባጭ መታቸው፤ የጌት ሰዎችም የውስጥ አካላቸውን ምስል ሠሩ፥
የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስዳችሁ በሰረገላው ላይ አኑሩአት፤ ስለበደል መባእ ካሳ አድርጋችሁ ያቀረባችሁትን የወርቁንም ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርጋችሁ በታቦቷ አጠገብ አኑሩት፤ ትሄድም ዘንድ ስደዱአት።
ወደምትሄድበትም ተመልከቱ፤ በድንበሩም መንገድ ላይ ወደ ቤትሳሚስ ብትወጣ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ያደረገብን እርሱ ነው፤ አለዚያም እንዲያው መጥቶብናል እንጂ የመታን የእርሱ እጅ እንዳልሆነ እናውቃለን።”