ዘፀአት 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ትክክለኛ ፍርድ 1 “ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ የዐመፅ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከዐመፀኛ ጋር አትቀመጥ። 2 ለዐመፅ ከብዙ ሰው ጋር አንድ አትሁን፤ ፍርድንም ለማጣመም ከብዙ ሰው ጋር አትጨመር። 3 በፍርድ ለድሀው አትራራ። 4 “የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው ፈጽሞ መልስለት። 5 የጠላትህን አህያ ከጭነቱ በታች ወድቆ ብታገኘው አትለፈው፤ ነገር ግን ከእርሱ ጋር ለማንሣት ርዳው። 6 “በፍርድ የድሀውን ፍርድ አታጣምም። 7 ከዐመፅ ፍርድ ሁሉ ራቅ፤ በደል የሌለበትንና ጻድቅን አትግደል፤ ኀጢአተኛውንም በመማለጃ አታድን፤ 8 መማለጃን አትቀበል፤ መማለጃ የዐይናማዎችን ዐይን ያሳውራልና፥ እውነተኛ ቃልንም ያጣምማልና። 9 በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች ዐውቃችኋልና። ሰባተኛው ዓመትና ሰባተኛው ቀን 10 “ስድስት ዓመት ምድርህን ዝራ፤ ፍሬዋንም አግባ፤ 11 በሰባተኛው ዓመት ግን ተዋት፤ አሳርፋትም፤ የሕዝብህም ድሆች ይበሉታል፤ እነርሱ ያስቀሩትንም የሜዳ እንስሳ ይብላው። እንዲሁም በወይንህና በወይራህ አድርግ። 12 ስድስት ቀን ሥራህን ሁሉ ሥራ፤ በሬህና አህያህ ያርፉ ዘንድ ለባሪያህም ልጅ ለመጻተኛውም ዕረፍት ይሆን ዘንድ በሰባተኛው ቀን ዕረፍ። 13 ያልኋችሁንም ነገር ሁሉ ጠብቁ፤ የሌሎችንም አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይሰማ። ሦስቱ ዐበይት በዓላት ( ዘፀ. 34፥18-26 ፤ ዘዳ. 16፥1-17 ) 14 “በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል አድርጉልኝ። 15 የቂጣውን በዓል ጠብቁ፤ በአዲስ ወር ከግብፅ ምድር ወጥታችኋልና በዚህ ወር እንዳዘዝኋችሁ ሰባት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ። 16 በፊቴ ባዶ እጅህን አትታይ። በእርሻም የምትዘራትን የፍሬህን በኵራት የመከር በዓል፥ ዓመቱም ሲያልቅ ፍሬህን ከእርሻ ባከማቸህ ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ። 17 በዓመት ሦስት ጊዜ በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ። 18 “የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የበዓሌም ስብ እስኪነጋ አይደር። 19 የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጣ። ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል። የተስፋዋን ምድር እንደሚወርሱ የተሰጠ ቃል ኪዳን 20 “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ፥ ወዳዘጋጀሁልህም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአኬን በፊትህ እልካለሁ። 21 ራስህን ጠብቅ፤ ስማው፤ እንቢም አትበለው፤ ስሜ በእርሱ ስለ ሆነ ይቅር አይልምና። 22 አንተ ግን ቃሌን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጥላቸዋለሁ፤ የሚቃወሙህንም እቃወማለሁ። 23 መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞሬዎናውያንም፥ ወደ ኬጤዎናውያንም፥ ወደ ፌርዜዎናውያንም፥ ወደ ከነዓናውያንም፥ ወደ ጌርጌሴዎናውያንም፥ ወደ ኤዌዎናውያንም፥ ወደ ኢያቡሴዎናውያንም ያገባሃል፤ እኔም አጠፋቸዋለሁ። 24 ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፤ አታምልካቸውም፤ እንደ ሥራቸውም አትሥራ፤ ነገር ግን ፈጽመህ አፍርሳቸው፤ ምስሎቻቸውንም ሰባብራቸው። 25 አምላክህንም እግዚአብሔርን ታመልካለህ፤ እኔ እህልህንና ወይንህን፥ ውኃህንም እባርካለሁ፤ በሽታንም ከአንተ አርቃለሁ። 26 በምድርህም መካን፥ ወይም የማይወልድ አይኖርም፤ የዘመንህንም ቍጥር እሞላለሁ። 27 በፊትህ መፈራትን እሰድዳለሁ፤ የምትሄድበትን ሕዝብ ሁሉ አስደነግጣቸዋለሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ እንዲሸሹልህ አደርጋለሁ። 28 በፊትህም ተርብ እሰድዳለሁ፤ አሞራዊውንም፥ ኤዌዎያዊውንም፥ ከነዓናዊውንም፥ ኬጤዎናዊውንም ከፊትህ ያባርራቸዋል። 29 ምድር ባድማ እንዳትሆን፥ የምድር አራዊትም እንዳይበዙብህ፥ በአንድ ዓመት አላባርራቸውም። 30 ነገር ግን እስክትበዛ፥ ምድርንም እስክትወርስ ድረስ ጥቂት በጥቂት አባርራቸዋለሁ። 31 ድንበርህንም ከኤርትራ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረ በዳም እስከ ታላቁ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ አሰፋለሁ፤ በምድር የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁና፤ ከአንተም አስወጣቸዋለሁ። 32 ከእነርሱና ከአማልክቶቻቸው ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ። 33 እኔን እንድትበድል እንዳያደርጉህ በሀገርህ ላይ አይቀመጡ፤ አማልክቶቻቸውንም ብታመልክ ወጥመድ ይሆኑብሃልና።” |