ዘሌዋውያን 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኀጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚቀርብባቸው ምክንያቶች 1 “አንድ ሰው ቢበድል፥ የሚያምለውንም ቃል ቢሰማ፥ ምስክርም ሆኖ አንድ ነገር አይቶ እንደ ሆነ፥ ወይም ዐውቆ እንደ ሆነ ያነን ባይናገር በደሉን ይሸከማል፤ 2 ርኩስ ነገርን፥ የሞተውን፥ አውሬ የነከሰውን፥ ወይም የበከተ፥ ወይም የሚንቀሳቀስ የእንስሳን በድን የነካ፥ ከእርሱም ያነሣ ሰው ቢኖር፤ 3 ወይም ርኩስነቱን ሳያውቅ ርኩስን ሰው ቢነካ፥ በማናቸውም ርኵሰት ቢረክስ፥ ነገሩ በታወቀ ጊዜ በደል ይሆንበታል። 4 ሰው ሳያስብ ክፉን ወይም መልካምን ያደርግ ዘንድ ሳያስብ በከንፈሩ ተናግሮ ቢምል፥ ሳያስብ የማለውም ከዚህ ባንዱ ነገር ቢሆን፥ በታወቀው ጊዜ ከዚህ ነገር በአንዱ በደለኛ ይሆናል። 5 ከእነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ቢሆን፥ የሠራውን ኀጢአት ይናዘዛል። 6 እግዚአብሔርን ስለ መበደሉና ስለ ሠራው ኀጢአት ከበጎቹ ነውር የሌለባትን እንስት በግ ወይም ከፍየሎች እንስት ፍየል ያመጣል፤ ካህኑም ስለ ኀጢአቱ ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል። 7 “ስለ ሠራው ኀጢአት የበግ መግዣ ገንዘብ በእጁ ባይኖረው ግን፥ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። ወደ ካህኑም ያመጣቸዋል፤ 8 ካህኑም አስቀድሞ ለኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ያቀርባል፤ ራሱንም ከአንገቱ ይቆለምመዋል፤ ነገር ግን አይቈርጠውም። 9 ከኀጢአቱም መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ግድግዳ ላይ ይረጨዋል፤ የተረፈውንም ደም ከመሠዊያው በታች ያንጠፈጥፋል፤ እርሱ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። 10 እንደ ሥርዐቱም ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያዘጋጀዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል። 11 “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ለማምጣት ገንዘብ በእጁ ባይኖረው፥ ስለ ሠራው ኀጢአት የኢፍ መስፈሪያ ዐሥረኛ ክፍል መልካም የስንዴ ዱቄት ለኀጢአት መሥዋዕት ያቀርባል፤ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና ዘይት አያፈስስበትም፤ ዕጣንም አይጨምርበትም። 12 ወደ ካህኑም ያመጣዋል፤ ካህኑም ስለ መታሰቢያው ለእርሱ እፍኝ ሙሉ ይዘግናል፤ ለእግዚአብሔርም በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል፤ እርሱም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 13 ካህኑም ከእነዚያ በአንዳቸው ስለ ሠራው ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል። የተረፈውም እንደ እህሉ ቍርባን ለካህኑ ይሆናል።” ስለ በደል መሥዋዕት 14 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 15 “ሰው ቢዘነጋ፥ ሳያውቅም ለእግዚአብሔር በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኀጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋዉ ነውር የሌለበትን እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን በብር ሰቅል የተገመተውን አውራ በግ ለበደል መሥዋዕት ያቀርባል። 16 በተቀደሰ ነገር ላይ ስለ ሠራው ኀጢአት ዕዳ ይከፍላል፤ አምስተኛውንም እጅ ይጨምርበታል፤ ለካህኑም ይሰጠዋል። ካህኑም በበደል መሥዋዕት አውራ በግ ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል። 17 “ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ ቢታወቀው፥ ኀጢአት ስለሆነችበትም ንስሓ ቢገባ፥ 18 ነውር የሌለበትን በሰቅል የተገመተውን አውራ በግ ከመንጋው ለበደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያመጣዋል፤ ካህኑም ሳያውቅ ስለ ሳተው ስሕተት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል። 19 እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ንስሓ ገብቶአልና።” |