ዘሌዋውያን 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2 “ሰው ኀጢአትን ቢሠራ፥ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ቸል ቢል፥ ያኖረበትን አደራ ወይም የኅብረትን ገንዘብ ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢሠራ፥ 3 ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ስለዚህም ቢዋሽ፥ ሰው ኀጢአትን ለመሥራት ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ በሐሰት ቢምል፥ 4 እርሱ ቢበድልና ከዚህ በኋላ ንስሓ ቢገባ፥ በቅድሚያ የወሰደውን፥ ወይም በዐመፅና በግፍ የተቀበለውን፥ ወይም የተሰጠውን አደራ፥ ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥ 5 ወይም በሐሰት የማለበትን ነገር ቢመልስ፥ በሙሉ ይመልስ፤ ከዚያም በላይ አምስተኛውን ክፍል ጨምሮ የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን ለባለ ገንዘቡ ይስጠው። 6 ስለ በደል መሥዋዕትም ከመንጋው ነውር የሌለበትን፥ ዋጋው እንደ በደሉ የተገመተውን አውራ በግ ለእግዚአብሔር ያምጣ።። 7 ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ስለዚያም ስለ አደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባልለታል።” ስለሚቃጠል መሥዋዕት ሕግ 8 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 9 “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ የሚቃጠለው የመሥዋዕቱ ሕግ ይህ ነው፤ የመሠዊያው እሳት በላዩ እየነደደች እስኪነጋ ትተዉታላችሁ። 10 ካህኑም የተልባ እግር ቀሚስና የተልባ እግር ሱሪ በሰውነቱ ላይ ይለብሳል፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል። 11 ልብሱንም ያወልቃል፤ ሌላም ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ንጹሕ ወደ ሆነ ስፍራ ወደ ውጭ ያወጣዋል። 12 እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፤ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ ዕንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል። 13 ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይነድዳል፤ አይጠፋም። ስለ እህል ቍርባን 14 “የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመሠዊያው ፊት ለፊት የሚያቀርቡት የመሥዋዕት ሥርዐት ይህ ነው። 15 ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መልካሙን የስንዴ ዱቄት ከዘይት ጋር እፍኝ ሙሉ፥ ደግሞም በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውን ዕጣን ሁሉ ያነሣል፤ ለእግዚአብሔርም በጎ መዓዛ ያለው የመታሰቢያ ቍርባን እንዲሆን ለመታሰቢያ ነውና በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። 16 ከእርሱም የተረፈውን አሮንና ልጆቹ ይበሉታል፤ ቂጣ ሆኖ በተቀደሰው ስፍራ ይበላል፤ በምስክሩ ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ ይበሉታል። 17 በእርሾ ቦክቶ አይጋገርም። ከእግዚአብሔር መሥዋዕት የሰጠኋቸው ዕድል ፈንታ ይህ ነው፤ እርሱም እንደ ኀጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 18 ከካህናት ወገን ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በዘመናችሁ ለዘለዓለም ሕግ ነው። ከሚቃጠለው የእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።” 19 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 20 “እርሱን በቀባህበት ቀን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የአሮንና የልጆቹ መባ ይህ ነው። የኢፍ መስፈርያ ዐሥረኛ ክፍል መልካሙን ዱቄት እኩሌታውን በጥዋት፥ እኩሌታውንም በማታ ለዘወትር መሥዋዕት ያቀርባሉ። 21 ከዘይት ጋር በምጣድ ላይ ያደርጉታል፤ ለውሰውም ያገቡታል፤ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚፈተት መሥዋዕት ነው። 22 ከልጆቹም በእርሱ ፋንታ የተቀባው ካህን ያቀርበዋል። ለዘለዓለም ሥርዐት ነው፤ ሁልጊዜም ይደረጋል። 23 ካህናትም የሚያቀርቡት የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠላል፤ ከእርሱም አንዳች አይበላም።” ስለ ኀጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት 24 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 25 “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የኀጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኀጢአቱ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል፤ እርሱም ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 26 የሚሠዋው ካህን ይበላዋል፤ በምስክሩ ድንኳን ዙሪያ በአለው አደባባይ በተቀደሰ ስፍራ ይበሉታል። 27 ሥጋውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤ ማናቸውም ልብስ ደም ቢረጭበት የተረጨበትን በተቀደሰ ስፍራ ያጥቡታል። 28 የሚቀቀልበትን ሸክላ ይሰብሩታል፤ በናስም ዕቃ ቢቀቀል ይፈገፍጉታል፤ በውኃም ያጥቡታል። 29 ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከእርሱ ይበላል፤ እርሱም ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 30 ነገር ግን በመቅደሱ ውስጥ ለማስተስረያ ይሆን ዘንድ ከደሙ ወደ ምስክሩ ድንኳን የሚገባው የኀጢአት መሥዋዕት ሁሉ አይበላም፤ በእሳት ይቃጠላል። |