1 ዜና መዋዕል 22:7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፥ “ልጄ ሆይ፥ እኔ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ልጄ ሆይ፤ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ለመሥራት በልቤ ዐስብ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ፦ “ልጄ ሆይ! እኔ ለአምላኬ ለጌታ ቤት እንድሠራ በልቤ አስቤ ነበር። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንዲህም አለው፤ “ልጄ ሆይ፥ እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቤ አስቤ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ “ልጄ ሆይ! እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር። |
ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፦ በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ሌሊትና ቀን የተገለጡ ይሁኑ።
እግዚአብሔርም አለው፥ “በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ እንደ ጸሎትህም ሁሉ አደረግሁልህ፤ ለዘለዓለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዐይኖችና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ።
አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ፤ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።”
ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቤት ስለ ወደድሁ፥ ለመቅደሱ ከሰበሰብሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና እነሆ፥ ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ።
እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘለዓለም እንደ ታዘዘው በእግዚአብሔር ፊት የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን ለማጠን፥ የገጹንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር በዓላት ለማቅረብ እኔ ልጁ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራለሁ፤ እርሱንም እቀድሳለሁ።
ስሙ በዚያ የሚኖር አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ፥ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፤ በትጋት ይፈጸም።”
በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ቍርባናችሁንም፥ ዐሥራታችሁንም፥ ከእጃችሁ ሥራ ቀዳምያቱን የተመረጠውንም መባችሁን ሁሉ፥ ለአምላካችሁም የተሳላችሁትን ሁሉ ውሰዱ።
አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራ ዘንድ የመረጠው ስፍራ ከአንተ ሩቅ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከላምና ከበግ መንጋህ እንዳዘዝሁህ እረድ፤ ሰውነትህም የወደደችውን በሀገርህ ውስጥ ብላው።
ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከከተሞቻችሁ ሁሉ በአንዱ ስሙ ይጠራ ዘንድ የመረጠውን ስፍራ ትሻላችሁ፤ ወደዚያም ትመጣላችሁ።