ዕዝራ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የቂሮስ ትእዛዝ መገኘት 1 በዚያ ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ በባቢሎን ቤተ መዛግብት ያሉ የታሪክ መጻሕፍት እንዲመረመሩ አዘዘ። 2 በሜዶን አውራጃ ባለው ባሪ በሚባል ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅልል ተገኘ፤ በውስጡም ይህ ነገር ለመታሰቢያ ተጽፎ ነበር። 3 በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ በኢየሩሳሌም ስላለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ አዘዘ፥ “ይህ ቤት ይሠራ መሥዋዕት የሚቀርብበትም ቦታ ይሠራ፤ ቁመቱም ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን። 4 በሦስት ተራ ታላላቅ ድንጋይ፥ በአንድ ተራ እንጨት ይደረግ፤ ወጭውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ። 5 ናቡከደነዖርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃ ይሰጥ፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ይኑር። የቤተ መቅደሱ ሥራ እንዲቀትል ንጉሥ ዳርዮስ ማዘዙ 6 “አሁንም አንተ በወንዝ ማዶ ያለኸው የሀገሩ ገዥ ተንትናይ ደግሞ አሰተርቡዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻችሁ አፈርስካውያን ከዚያ ራቁ፤ 7 ይህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ ተዉ፤ የአይሁድም አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው ይሥሩ። 8 ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን፥ በወንዝ ማዶ ካለው ሀገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጭውን በትጋት እንድትሰጡአቸው፥ ሥራም እንዳታስፈቱአቸው አዝዣለሁ። 9 ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን ወይፈኖችና አውራ በጎች፥ ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌምም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው፥ የወይን ጠጅና ዘይት የሚጠይቋችሁን ዕለት ዕለት ስጡአቸው። 10 ይኸውም ለሰማይ አምላክ በጎ መዓዛ የሆነውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ለንጉሡና ለልጆቹም ዕድሜ ይጸልዩ ዘንድ ነው። 11 ይህንም ትእዛዝ የሚለውጥ ሁሉ ምሰሶው ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰቀልበት፤ በላዩም ይገደል፤ ቤቱም የጕድፍ መጣያ ይደረግ ብዬ አዝዣለሁ። 12 ስሙ በዚያ የሚኖር አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ፥ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፤ በትጋት ይፈጸም።” የእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ 13 ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ ደግሞ አስተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም እንዲሁ ተግተው አደረጉ። 14 የአይሁድ ሽማግሌዎችና ሌዋውያንም በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት መሠረት ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤልም አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስና እንደ ዳርዮስ፥ እንደ አርተሰስታም ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። 15 ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። 16 የእስራኤልም ልጆች ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ የቀሩትም የምርኮኞች ልጆች የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ። 17 በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች፥ አራት መቶም የበግ ጠቦቶች አቀረቡ፤ ስለ ኀጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። 18 በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው፥ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው አቆሙ። 19 የምርኮኞቹም ልጆች በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ። 20 ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሓን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ልጆች ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸው ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም የፋሲካውን በግ ዐረዱ። 21 ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ ፋሲካውን በሉ፤ 22 እግዚአብሔርም ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ። |