1 ነገሥት 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ለሰሎሞን ዳግመኛ እንደ ተገለጠለት ( 2ዜ.መ. 7፥11-22 ) 1 ከዚህም በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን ያደርገው ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ 2 እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። 3 እግዚአብሔርም አለው፥ “በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ እንደ ጸሎትህም ሁሉ አደረግሁልህ፤ ለዘለዓለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዐይኖችና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። 4 ዳዊትም አባትህ በጽድቅ፥ በንጹሕ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዐቴንም ሕጌንም ብትጠብቅ፥ 5 እኔ፦ በእስራኤል ላይ የሚገዛ ሰውን ከአንተ አላጠፋም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጸናለሁ። 6 ነገር ግን እናንተና ልጆቻችሁ እኔን ትታችሁ ወደ ኋላ ብትመለሱ ለሙሴ በፊታችሁ የሰጠሁትን ትእዛዜንና ሥርዐቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ 7 እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ለጥፋትና ለተረት ይሆናሉ። 8 ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ፦ እግዚአብሔር በዚህ ሀገርና በዚህ ቤት ስለ ምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል። 9 መልሰውም፦ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።” ያንጊዜም ሰሎሞን የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ አውጥቶ በዚያ ወራት ለራሱ በሠራው ቤት አስገባት። 10 ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ሁለቱን ቤቶች በሠራበት በሃያ ዓመት ውስጥ፥ 11 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም በዝግባና በጥድ እንጨት፥ በወርቅና በሚሻውም ሁሉ ሰሎሞንን ረድቶት ነበር። ያንጊዜም ንጉሡ ሰሎሞን በገሊላ ምድር ያሉትን ሃያ ከተሞች ለኪራም ሰጠው። 12 ኪራምም ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ያይ ዘንድ ከጢሮስ ወጣ፤ ወደ ገሊላም ሄደ፤ ደስም አላሰኙትም። 13 እርሱም አለው፥ “ወንድሜ ሆይ! የሰጠኸኝ እነዚህ ከተሞች ምንድን ናቸው?” እስከ ዛሬም ድረስ ወሰን ብሎ ጠራቸው። 14 ኪራምም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ለሰሎሞን አመጣ። 15 ንጉሡም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና ቤተ መንግሥቱን፥ ሜሎንንም፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር፥ አሶርንም፥ መጊዶንም፥ ጋዜርንም ይሠራ ዘንድ ሠራተኞችን መልምሎ ነበር። 16 የግብፅም ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጋዜርን ያዘ፤ በእሳትም አቃጠላት፤ በሜርጎብ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያንንም ገደላቸው፤ ለልጁም ለሰሎሞን ሚስት እነዚያን አገሮች ትሎት አድርጎ ሰጥቶአት ነበር። 17 ሰሎሞንም ጋዜርንና የታችኛውን ቤቶሮንን፥ ባዕላትንም ሠራ፤ 18 በምድረ በዳ ሀገር ያለችውን ኤያቴርሞትን ሠራ፤ 19 ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፤ የሰረገላውንም ከተሞች፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም፥ በሊባኖስም፥ በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ። 20 ከእስራኤልም ልጆች ዘንድ ያልነበሩትን ከአሞሬዎናውያንና ከኬጤዎናውያን፥ ከከናኔዎን፥ ከፌርዜዎናውያን፥ ከኤዌዎናውያን፥ ከኢያቡሴዎናውያንና ከጌርጌሴዎናውያን፥ የቀሩትን አሕዛብ ሁሉ፥ ከእነርሱም በኋላ በምድሪቱ የቀሩትን፥ 21 የእስራኤልም ልጆች ያጠፉአቸው ዘንድ ያልቻሉትን፥ ልጆቻቸውን ሰሎሞን እሰከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። 22 ሰሎሞንም ከእስራኤል ልጆች ማንንም ገባር አላደረገም፤ እነርሱ ግን ተዋጊዎች፥ ሎሌዎችም፥ መሳፍንትም፥ አለቆችም፥ የሰረገሎችና የፈረሶች ባልደራሶች ነበሩ። 23 ሰሎሞንም በሚሠራው ሥራ ላይ ሠራተኛውን ሕዝብ የሚያዝዙ አለቆች አምስት መቶ አምሳ ነበሩ። 24 የፈርዖንንም ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ወደ ቤቷ አመጣት፤ በዚያ ጊዜም ሚሎንን ሠራት። 25 ሰሎሞንም በየዓመቱ ሦስት ጊዜ የሚቃጠለውንና የሰላሙን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በሠራው መሠዊያ ላይ ያሳርግ ነበር፤ በእግዚአብሔርም ፊት ባለው መሠዊያ ላይ ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ ቤቱንም ጨረሰ። 26 ንጉሡም ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር በኤርትራ ባሕር ዳር በኤላት አጠገብ ባለችው በጋሴዎንጋቤር መርከቦችን ሠራ። 27 ኪራምም በእነዚያ መርከቦች ከሰሎሞን አገልጋዮች ጋር ባሕሩን መቅዘፍ የሚያውቁ መርከበኞች አገልጋዮቹን ላከ። 28 ወደ አፌርም ደረሱ፤ ከዚያም አራት መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ወሰዱ፤ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞንም ይዘው አገቡ። |