ዳንኤል 7:14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በልዩ ልዩ አገር የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ያገለግሉት ዘንድ ሥልጣን፥ ክብርና ንጉሥነት ተሰጠው፤ ግዛቱም የማይጠፋ ዘለዓለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፥ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው። |
ሕፃን ተወልዶልናል፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል ይባላል።
ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።
ወዲያውኑም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው፤ ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ።
“በእነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
ከዚያም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ የሚል ዐዋጅ ታወጀ፤ “ሕዝቦች ሆይ፤ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ እንድታደርጉ የታዘዛችሁት ይህ ነው፤
“በማንኛውም የመንግሥቴ ግዛት ሰው ሁሉ፣ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር ይህን ዐዋጅ አውጥቻለሁ። “እርሱ ለዘላለም የሚኖር፣ ሕያው አምላክ ነውና፣ መንግሥቱ አይጠፋም፤ ለግዛቱም መጨረሻ የለውም።
ከዚያም ከሰማይ በታች ያሉ መንግሥታት ልዕልና፣ ሥልጣንና ታላቅነት ለልዑሉ ሕዝብ፣ ለቅዱሳን ይሰጣል። መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ይሆናል፤ ገዦች ሁሉ ያመልኩታል፤ ይታዘዙታልም።’
የሽባዎችን ትሩፍ፣ የተገፉትንም ብርቱ ሕዝብ አደርጋለሁ፤ ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
“ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም።
“ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ደግሞም ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብ ማን እንደ ሆነም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ የለም።”
ሕዝቡም፣ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕግ ሰምተናል፤ ታዲያ፣ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ ‘የሰው ልጅ’ ማን ነው?” አሉት።
ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤
ሰባተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፤ “የዓለም መንግሥት፣ የጌታችንና የርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤ እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”
እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉ ግን ድል ይነሣቸዋል፤ ምክንያቱም እርሱ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው፤ ከርሱ ጋራ ያሉ የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም ዐብረው ድል ይነሣሉ።”