መዝሙር 103 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 103 የዳዊት መዝሙር። 1 ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ የውስጥ ሰውነቴም ሁሉ ቅዱስ ስሙን ባርኪ። 2 ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ ውለታውንም ሁሉ አትርሺ፤ 3 ኀጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፣ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፣ 4 ሕይወትሽን ከጥፋት ጕድጓድ የሚያድን፣ ምሕረትንና ርኅራኄን የሚያቀዳጅሽ፣ 5 ጕልማሳነትሽም እንደ ንስር ይታደስ ዘንድ፣ ምኞትሽን በበጎ ነገር የሚያረካ እርሱ ነው። 6 እግዚአብሔር ለተጨቈኑ ሁሉ፣ ቅን ፍርድንና ፍትሕን ይሰጣቸዋል። 7 መንገዱን ለሙሴ፣ ሥራውንም ለእስራኤል ሕዝብ አሳወቀ። 8 እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ታማኝነቱም የበዛ ነው። 9 እርሱ ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም፤ ለዘላለምም አይቈጣም። 10 እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። 11 ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት። 12 ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ። 13 አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። 14 እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል። 15 ሰው እኮ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ ያቈጠቍጣል፤ 16 ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ድራሹ ይጠፋል፤ ምልክቱም በቦታው አይገኝም። 17 የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤ 18 ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣ ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጕት ላይ ይሆናል። 19 እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቷል፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች። 20 እናንተ ለቃሉ የምትታዘዙ መላእክቱ፣ ትእዛዙንም የምትፈጽሙ እናንተ ኀያላን፤ እግዚአብሔርን ባርኩ። 21 እናንተ ፈቃዱን የምትፈጽሙ አገልጋዮቹ፣ ሰራዊቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። 22 እናንተ በግዛቱ ሁሉ የምትኖሩ፣ ፍጥረቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.