መዝሙር 146 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 146 1 ሃሌ ሉያ። ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ። 2 በምኖርበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ለአምላኬ እዘምራለሁ። 3 በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችም አትመኩ። 4 መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል። 5 ብፁዕ ነው፤ ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣ ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው፤ 6 እርሱ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ የፈጠረ፣ ታማኝነቱም ለዘላለም የሆነ ነው፤ 7 ለተበደሉት የሚፈርድ፣ ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው፤ እግዚአብሔር እስረኞችን ከእስራት ያወጣል፤ 8 እግዚአብሔር የዕውራንን ዐይን ያበራል፤ እግዚአብሔር የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ 9 እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድኻ አደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤ የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል። 10 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽ ለትውልድ ሁሉ ንጉሥ ነው። ሃሌ ሉያ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.