መዝሙር 145 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 145 የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 አምላኬና ንጉሤ ሆይ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህን ከዘላለም እስከ ዘላለም እባርካለሁ። 2 በየቀኑ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ከዘላለም እስከ ዘላለም አመሰግናለሁ። 3 እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤ ታላቅነቱም አይመረመርም። 4 ሥራህን አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ ያስተጋባል፤ ብርቱ ሥራህን ያውጃል። 5 ስለ ግርማህ ውበትና ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ድንቅ ሥራህም ያወራሉ። 6 ስለ ድንቅ ሥራህ ብርታት ይነጋገራሉ፤ እኔም ስለ ታላቅነትህ ዐውጃለሁ። 7 የበጎነትህን ብዛት በደስታ ያወሳሉ፤ ስለ ጽድቅህም በእልልታ ይዘምራሉ። 8 እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ታማኝነቱም የበዛ ነው። 9 እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው። 10 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍጥረትህ ሁሉ ያመሰግንሃል፤ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል። 11 ስለ መንግሥትህ ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ኀይልህም ይነጋገራሉ፤ 12 በዚህም ለሰው ልጆች ብርቱ ሥራህን፣ የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ። 13 መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፤ ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል። እግዚአብሔር ቃሉን ሁሉ ይጠብቃል፤ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። 14 እግዚአብሔር የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤ የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል። 15 የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል፤ አንተም ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸዋለህ። 16 አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ። 17 እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ፣ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። 18 እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። 19 ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም። 20 እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ክፉዎችን ሁሉ ግን ያጠፋል። 21 አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ፍጡር ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ቅዱስ ስሙን ይባርክ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.