ራእይ 9:20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በእነዚህ መቅሠፍቶች ከሞት የተረፉት የሰው ዘር ከእጃቸው ሥራ ተመልሰው ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትንና ከወርቅ፥ ከብር፥ ከናስ፥ ከድንጋይና ከእንጨት የተሠሩ ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን ጣዖቶች ማምለክንም አልተዉም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በእነዚህ መቅሠፍቶች ሳይገደሉ የቀሩት ሰዎች አሁንም ከእጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትን እንዲሁም ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን፣ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከናስ፣ ከድንጋይና ከዕንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች ማምለክ አልተዉም፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ስለ እጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ ለአጋንንትና ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶችም መስገድን አልተዉም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤ |
እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ ይህም ያደረጉት በደል ቊጣዬን አነሣሥቶአል፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተነሣሣው ቊጣዬም ይፈጸማል እንጂ አይበርድም፤
የእጅ ጥበብ ዐዋቂው ወርቅ አንጥረኛን ያበረታታዋል፤ ጣዖት ጠርቦ በመዶሻ የሚያለሰልሰውም በመስፍ ላይ የሚመታውን ‘አይዞህ በርታ! ብየዳው መልካም ነው!’ ይለዋል። እንዳይንቀሳቀስም ጣዖቱን በምስማር ይቸነክሩታል።”
ሌሎች አማልክትን አትከተሉ፥ አታገልግሉአቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ በእጃችሁ ለሠራችኋቸው ጣዖቶች በመስገድ እግዚአብሔርን ለቊጣ አታነሣሡ፤ ይህን ትእዛዝ ብትጠብቁ እርሱ አይቀጣችሁም።’
መጥታችሁ በምትኖሩባት በዚህችስ በግብጽ ምድር ለጣዖቶች በመስገድና ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ስለምን ታስቈጡኛላችሁ? ወይስ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እንዲዘባበቱባችሁና ስማችሁንም መራገሚያ ያደርጉት ዘንድ ራሳችሁን በራሳችሁ ማጥፋት ትፈልጋላችሁን?
እግዚአብሔር ሆይ ዐይኖችህ እውነትን የሚመለከቱ አይደሉምን? አንተ ቀሠፍሃቸው፤ እነርሱ ግን ከምንም አልቈጠሩትም፤ አደቀቅሃቸው፤ እነርሱ ከስሕተታቸው መማር እምቢ አሉ፤ እልኸኝነትን አበዙ እንጂ፥ ከኃጢአታቸው መመለስ አልፈለጉም።
ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ ከቤተ መቅደሱ ተዘርፈው የመጡትን የወርቅ ዕቃዎች አስመጥተህ አንተና መኳንንቶችህ፥ ሚስቶችህና ቁባቶችህ የወይን ጠጅ መጠጫ አደረጋችኋቸው፤ ከጠጣችሁም በኋላ ማየት ወይም መስማት የማይችሉትንና ምንም ነገር የማያውቁትን ከወርቅ፥ ከብር፥ ከነሐስ፥ ከብረት፥ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገናችሁ፤ መግደል ወይም ማዳን የሚችለውንና አካሄድህን የሚቈጣጠረውን ሕያው አምላክ ግን አላከበርከውም።
የእስራኤል ሕዝብ ከእምነታቸው ለሚያርቁአቸው አጋንንት መሥዋዕት አድርገው እንስሶቻቸውን በየሜዳው በማረድ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ አይገባቸውም፤ እስራኤላውያን ይህን ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ይጠብቁት።
መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ቢመጣ አላመናችሁትም፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ ይህንንም አይታችሁ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም።”
እንግዲህ እኛ የእርሱ ልጆች ከሆንን ‘እግዚአብሔር በሰው ጥበብና አሳብ ከወርቅ ወይም ከብር ወይም ከድንጋይ የተሠራውን ቅርጽ ይመስላል’ ብለን ማሰብ አይገባንም።
ይህ ጳውሎስ ‘በሰው እጅ የተሠሩ ምስሎች አማልክት አይደሉም’ እያለ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት አገሮች በቀር በመላዋ እስያ ምን ያኽል ብዙ ሕዝብ እንዳግባባና እንዳሳመነ እናንተ ራሳችሁ ያያችሁትና የሰማችሁት ነው።
እንደገና ወደ እናንተ ስመጣ አምላኬ ምናልባት በእናንተ ፊት ያዋርደኛል ብዬ እፈራለሁ፤ ከዚህ ቀደም ኃጢአት ሠርተው በዚሁ በሠሩት ርኲሰት፥ ዝሙትና፥ ስድነት ንስሓ ስላልገቡት ሰዎች ሐዘን ላይ እወድቃለሁ ብዬ እፈራለሁ።
እኔ ከሞትሁ በኋላ ካዘዝኳቸው ትእዛዝ በመውጣት የርኲሰትን ሥራ እንደሚፈጽሙ ዐውቃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ በመሥራት ስለሚያስቈጡት መቅሠፍት ያመጣባቸዋል።”
ከዚህ በፊት ላላወቁአቸው፥ በቅርቡ አዲስ ለመጡ፥ ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት የቀድሞ አባቶቻቸው ላላመለኩአቸው አማልክት መሥዋዕት አቀረቡ።
እዚያም፥ ለማየት፥ ለመስማት፥ ለመብላትና ለማሽተት የማይችሉትንና ከእንጨትና ከድንጋይ በሰው እጅ የተሠሩትን ሌሎች አማልክትን ታመልካላችሁ።
መንፈስ ቅዱስ ግን በግልጥ እንዲህ ይላል፤ “በኋለኛው ዘመን አንዳንድ ሰዎች አሳሳች መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት በመከተል ሃይማኖትን ይክዳሉ።”
ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ቊጣ የሚፈጸምባቸውን የመጨረሻ የሆኑትን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙትን ሰባት መላእክት አየሁ።