ማቴዎስ 25:31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “የሰው ልጅ በመላእክቱ ሁሉ ታጅቦ በክብር ሲመጣ በክብር ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋራ በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ |
እናንተም ተራራውን በሁለት ከፍሎ እስከ አጻል በደረሰው በዚህ ሸለቆ ውስጥ አልፋችሁ ታመልጣላችሁ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያ ዘመን ምድር በተናወጠች ጊዜ የቀድሞ አባቶቻችሁ በሸሹት ዐይነት ትሸሻላችሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬም ቅዱሳኑን አስከትሎ ይመጣል።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጅ በክብር ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት በአዲሱ ዓለም የእኔ ተከታዮች የሆናችሁ፥ እናንተም፥ በዐሥራ ሁለት ዙፋኑ ላይ ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ እንዳልከው ነው፤ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታዩታላችሁ፤ እንዲሁም በሰማይ ደመና ሆኖ ሲመጣ ታዩታላችሁ እላችኋለሁ።”
በዚህ በከሐዲና በኃጢአተኛ ትውልድ ፊት በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ እኔም የሰው ልጅ በአባቴ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር ስመጣ በእርሱ አፍርበታለሁ።”
በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም በራሱ ክብርና በአባቱ ክብር፥ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።
“እናንተ የገሊላ ሰዎች፥ ስለምን ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ቆማችኋል? ይህ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፥ ወደ ሰማይ ሲያርግ ባያችሁት ዐይነት ተመልሶ ይመጣል” አሉአቸው።
በዚህ ዐይነት ጌታችን ኢየሱስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር በሚመጣበት ጊዜ በአምላካችንና በአባታችን ፊት ልባችሁ ነቀፋ የሌለበትና ቅዱስ እንዲሆን ያበረታችኋል።
የትእዛዝ ድምፅ፥ የመላእክት አለቃ ድምፅ፥ የእግዚአብሔር እምቢልታም ይሰማል፤ ጌታ ራሱም በእነዚህ ታጅቦ ከሰማይ ይወርዳል፤ በክርስቶስ አምነው የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ።
እንዲሁም ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ለማስወገድ አንድ ጊዜ ተሠውቶአል፤ ደግሞም ኃጢአትን ለመሸከም ሳይሆን እርሱን የሚጠባበቁትን ለማዳን ሁለተኛ ጊዜ ይገለጣል።
ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሔኖክ ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦ “እነሆ እግዚአብሔር እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር ሆኖ በሁሉም ላይ ለመፍረድ ይመጣል፤
እነሆ በደመና ይመጣል፤ የወጉት ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ሰው ሁሉ ያየዋል፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ምክንያት ያለቅሳሉ፤ ይህ ነገር እውነት ነው፤ አሜን።
እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ይደመሰሳሉ፤ ከሰማይም ያንጐደጒድባቸዋል፤ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ይፈርዳል፤ ለንጉሥም ኀይልን ይሰጠዋል፤ ለመረጠውም ክብሩን ከፍ ከፍ ያደርግለታል።”